
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወንጀል መከላከል፣ የምርመራ እና የመረጃ አሰባሰብ አሠራሮች በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ እያከናወነ መኾኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና መምሪያ ኅላፊ ሙሊሳ አብዲሳ በወንጀል ምርመራ እና በመከላከል ረገድም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አሠራሮች በስፋት እየተተገበሩ መኾኑን ገልጸዋል። በወንጀል መከላከል ሂደት የፖሊስ እና ኅብረተሰቡ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ተጨባጭ ለውጥ ስለማምጣቱም ኅላፊው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የተለያዩ የወንጀል ሙከራዎችን በማክሸፍ እና አጥፊዎችንም በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል ለሕግ ማቀረብ የተቻለው በፖሊስ እና ሕብረተሰቡ የተባበረ ሥራ መኾኑን አስረድተዋል። በወንጀል መከላከል፣ በምርመራ እና በመረጃ አሰባሰብ ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮች በስፋት እየተተገበሩ መኾኑም የፖሊስን ሥራ ፈጣን እና ዘመናዊ አድርጎታል ብለዋል።
በቀጣይነትም የፖሊስን አሠራር ይበልጥ የማዘመን ሥራዎች እንደሚቀጥሉ የተናገሩት መምሪያ ኅላፊው የኅብረተሰቡ ትብብር እና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!