
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት ምሽት 1፡00 ጀምሮ በባሕር ዳር ቁ.2 የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ በተዘረጋ 15 ኪሎ ቮልት ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ኬብል ላይ ጉዳት ደርሷል።
በዚህ መሰረት በአየር ኀይል፣ በመኮድ፣ በአየር መንገድ፣ በውኃ ጉድጓዶች፣ በቀበሌ 14 እና 16 ባሉ ፋብሪካዎች፣ በቀበሌ 13፣ 14 እና 16 እንዲሁም በአሚኮ፣ በወገልሳ፣ በዘጌ፣ በላታ፣ በጭንባ፣ በይባብ፣ በመራዊ እና አካባቢዎቻቸው የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደተቋረጠ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳውቋል።
የተቋረጠውን አቅርቦት ለመመለስ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል። በአካባቢዎቹ የሚገኙ ደንበኞች ይህንን ተገንዝበው በትግስት እንዲጠብቁም ተቋሙ አሳስቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!