
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሀገር በሚሰጠው ልዩ የክረምት ወራት የመምህራን ብቃት ማሻሻያ ሥልጠና መክፈቻ ላይ በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ታዳጊዎች ሀገርን በመውደድ ስሜት ሙሉ ሁነው እንዲያድጉ እና ሀገር ፀንታ እንድትቆይ የመምህራን ሚና ከፍ ያለ ነው” ብለዋል። ትውልድ ላይ የሚሠሩ መምህራንን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል።
በመላው ሀገሪቱ ያሉ ከ60ሺህ በላይ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ልዩ የክረምት ብቃት ማሻሻያ ሥልጠናውን በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ከሐምሌ 23/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚወስዱም የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሥልጠናው እንደሀገር በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ እና የመምህራን የወደፊት ዕድገትን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሦሥት ዓመታትም በመላው ሀገሪቱ ያሉ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ሁሉ በዚህ የሥልጠና ሂደት እንዲያልፉ ይደረጋልም ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!