“አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ አማራጮችን ሁሉ ማየት ይገባል” የምክር ቤት አባላት

35

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ከሰዓት በኋላም ቀጥሏል፡፡ ከሰዓት በፊት በነበረው የጉባኤው ውሎ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመንግሥታቸውን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ከርእሰ መሥተዳድሩ የአፈጻጸም ሪፖርት በኋላ የምክር ቤት አባላቱ ለአሥፈጻሚ አካል ጥያቄ እና አስተያየት እያቀረቡ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ክልሉ በግጭት ውስጥም ኾኖ ያከናዎናቸው ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ተግባራት ተስፋ ሰጭ ናቸው ብለዋል፡፡ የክልሉ ሰላም ተጠብቆ በሙሉ አቅም ወደ ልማት ፊታችንን ብናዞር ከዚህ የተሻለ አፈጻጸም ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ አጽንኦት ሰጥተው ባነሱት የክልሉ ሰላም ዙሪያ የክልሉ መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ያሳየውን ተነሳሽነት በጎ እርምጃ ብለውታል፡፡ ለተፈጻሚነቱ ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ መሥራት እንደሚጠይቅም አንስተዋል፡፡ “አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ ሕጋዊ አማራጮችን ሁሉ ማየት ይገባል” ያሉት የምክር ቤት አባላቱ የታጠቁ ኀይሎችም ለክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ሲሉ የሰላም አማራጮችን ተቀብለው መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ክልሉ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ እና የክልሉን ሕዝብ አንድነት የሚሸረሽሩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ትንኮሳዎችም እንዲቆሙ የምክር ቤት አባላቱ ጠይቀዋል፡፡ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚስተዋሉ ምጣኔ ሃብታዊ እና የሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች የክልሉ መንግሥት በሚችለው ልክ ቢፈታ የሚል ጥያቄ ያቀረቡት የምክር ቤት አባል ነገር ግን ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጣጠል በሚሞክሩ ኀይሎች ላይ ክልሉ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

አሥፈጻሚው አካል የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ አሁን ካለው አቅም ባለፈ ጥረት ቢያደርግ ያሉት የምክር ቤቱ አባላት የግል ፍላጎታቸውን በሕዝብ ስም ለማስፈጸም የሚሞክሩ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የመሠረተ ልማት፣ የመብራት እና ሌሎች የሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ፈቃድ እንዲሁም የፈቃድ ዕድሳት አሰጣጥ መመሪያ ወጣ፡፡
Next article“ታዳጊዎች ሀገርን በመውደድ ስሜት ሙሉ ኾነው እንዲያድጉ የመምህራን ሚና ከፍ ያለ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)