ኅብረተሰቡ ከጎርፍ እና ውኃ ሙሌት አደጋዎች ራሱን እንዲጠብቅ መንግሥት አሣሠበ።

42

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባስነበበው የጥንቃቄ መልእክት ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአንድ አንድ የሀገራችን አካባቢዎች በደረሱ የመሬት መንሸራተት እና የውኃ ሙሌት ምክንያት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፋን እና በንብረትም ላይ አደጋ መከሰቱን አስታውሷል፡፡

በትናንትናው ምሽት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ ጉዱ ሞና ሆሞ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአካል ጉዳት እና የንብረት መውደም አደጋም ደርሷል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጓዙ በነበሩት ሰዎች ላይ በውኃ ሙሌት ምክንያት በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በደረሱ አደጋዎች ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል፡፡

ወቅቱ የክረምት ወቅት መኾኑን በመገንዘብ ለመሰል አደጋዎች ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያድርጉ መንግሥት አሣሥቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምድረ ቀደምት እና የነፃነት ተምሳሌት የኾነችውን ኢትዮጵያ የዓለም የጎብኝዎች ማዕከል ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next articleየከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ፈቃድ እንዲሁም የፈቃድ ዕድሳት አሰጣጥ መመሪያ ወጣ፡፡