
አዲስ አበባ: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሉሲ የተገኘችበት ግማሽ ምዕተ ዓመት ፕሮግራም በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተከብሯል። በኢትዮጵያ በርካታ የአርኪዎሎጂ ምርምሮች ተደርገው የተለያዩ ግኝቶች ቢመዘገቡም የሰው ልጅ አመጣጥ ታሪክ መስመርን ያስቀየረችው ግን እ.አ.አ በ1974 በኢትዮጵያ አፋር ክልል ሃዳር በተሰኘ ቦታ የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪት አካል መገኘት ነው።
የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ግኝት ግማሽ ምዕተ ዓመት መታሰቢ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል ሙዚየም የተከበረ ሲኾን ሉሲን ያገኙት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆንሰንም ተገኝተዋል። ተመራማሪው ሲናገሩ “እኛ የሰው ልጆች ምንም እንምሰል፣ የትም እንኑር መነሻችን ኢትዮጵያ መኾኗን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል። የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ዓለም ያደንቃል፤ ለዚህ ምክንያቱ የሰው ዘር መገኛ መኾኗ ነው ብለዋል አንትሮፖሎጂስቱ ፕሮፌሰር ጆንሰን።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ፕሮግራሙን አስመልክቶ ሲናገሩ ፕርግራሙን ማዘጋጀት ያስፈለገው ኢትዮጵያ ትክክለኛ የሰው ልጅ መገኛ እና ምድረ ቀደምት መኾኗን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በአግባቡ ሰንዶ ለዓለም ማስረዳት አስፈላጊ ስለኾነ ነው ብለዋል። በመድረኩ የታደሙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምድረ ቀደምት እና የነፃነት ተምሳሌት የኾነችውን ኢትዮጵያ የዓለም የጎብኚዎች ማዕከል ለማድረግ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሉሲን ያገኙትን አትሮፖሎጅስት ፕሮፌሰር ጆንሰን እና ከ ሰላሳ ግኝቶች አራቱን ያገኙትን ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዮሃንስ ኃይለሥላሴን አመሠግነዋል። ወደፊትም በተመራማሪዎቻችን በኢትዮጵያ ተጨማሪ ግኝቶች እንደሚመዘገቡ ተስፋ አለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!