በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የሚያስችሉ ተደጋጋሚ ውይይቶች መካሄዳቸውን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

58

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ረፋድ ውሎም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥታቸው ያከናወናቸውን ተግባራት ዓመታዊ ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው፡፡

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ክልሉ የሰላም እጦት ችግር ገጥሞት እንደ ቆየ የገለጹት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሰላም እጦቱ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶችን አስከትሏል ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን የሰላም እጦት ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ተደጋጋሚ ሕዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ። የተካሄዱት ተደጋጋሚ ውይይቶችም ሕዝቡ የችግሩን አሳሳቢነት እና የተሳሳተ መንገድ እንዲረዳ ረድቶታል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ የክልሉ ሕዝብ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾን እና ከነበረበት ድንግርግር ሁኔታ እንዲወጣ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የልዩ ኀይል መልሶ ማደራጀትን በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ አዛብተው በማቅረብ ክልሉን ለአንድ ዓመት በዘለቀ ግጭት ውስጥ እንዲቆይ አድርገውታል ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተፈጠረው ውዥንብር ከተበተኑ የልዩ ኀይል አባላት በርካቶቹ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖችም የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው የክልሉን የፀጥታ መዋቅር መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሕግ ከማስከበር ሥራው ጎን ለጎን የክልሉን የፀጥታ መዋቅር እንደገና በማደራጀት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሕዝቡም የሰላሙ ባለቤት በመኾን ማገዝ መጀመሩ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ሰላማዊ በኾነ መንገድ ለመቋጨት በሰላም ካውንስሉ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ እና መላው የክልሉ ሕዝብ ለሰላማዊ አማራጮቹ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት ድረስ እየከፈሉ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉ ለክልሉ የፀጥታ መዋቅር፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች እና ለመላው የክልሉ ሕዝብ በክልሉ መንግሥት ስም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ መዳረሻውን ወደ 139 ማሳደጉን ገለጸ።
Next articleምድረ ቀደምት እና የነፃነት ተምሳሌት የኾነችውን ኢትዮጵያ የዓለም የጎብኝዎች ማዕከል ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ገለጹ።