“የተሻለ የገበያ ማረጋጋት ሥራን ለመሥራት የንግዱ ማኅበረሰብ አጋዥ ኃይል ሊኾን ይገባል” የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር

11

ደሴ: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረውን የ2016 ዓ.ም የንግድ ቀን እያከበረ ነው። የኑሮ ዉድነቱን ከማረጋጋት አንጻር በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎች በመድረኩ ላይ ቀርበው ውይይትም ተደርጓል። የሸማቾች ማኅበራት፣ ነጋዴዎች፣ የከተማ እና የክፍለ ከተማ መሪዎች የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።

የከተማው ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሠራቸው ሥራዎች መልካም መኾናቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡ አሁን ካለው በተሻለ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባ እና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ተገቢውን ሕግ የማስከበር ሥራ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡

መምሪያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዕቅድ በማቀድ እና ወደ ክፍለ ከተማ በማውረድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ ገልጸዋል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አኳያ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት አመሥግነዋል፡፡ “የተሻለ የገበያ ማረጋጋት ሥራን ለመሥራት የንግዱ ማኅበረሰብ አጋዥ ኃይል ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት።
በመድረኩ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያቀርቡ ለነበሩ ሸማቾች፣ ፋብሪካዎች እና ክፍለ ከተሞች ዕውቅና ተሠጥቷል።

ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምጣኔ ሃብታዊ እድገቱ እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ግብርና የማይተካ ሚና ስላለው ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ መዳረሻውን ወደ 139 ማሳደጉን ገለጸ።