
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ጀምሯል፡፡ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን መንግሥት ዓመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት እያቀረቡ ነው፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ሰፊ ችግሮችን ማስከተሉን ጠቅሰው በበርካታ ዘርፎች አፈጻጸምም ላይም ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሁሉም ተቋማት በችግር ውስጥም ኾነው ዓመታዊ እቅዳቸውን ለመፈጸም ብርቱ ጥረት እንዳደረጉም ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ተቋማት ደግሞ የተሻለ አፈጻጸም ስለማስመዝገባቸው ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከክልሉ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳደሩ ምርት እና ምርታማነትን ለማሻሻል በችግር ውስጥም ኾነን ካለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ ግብዓት ማድረስ ችለናል ብለዋል፡፡ በምርት ዘመኑ የታቀደውን ምርት ለማግኘት በሚያስችል መልኩ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ዘርፍ አሁንም ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ችግር አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ልክ እንዳያመርቱ፣ ያመረቱትን ከቦታ ቦታ በተፈለገው መጠን እንዳያንቀሳቅሱ እና ግብዓት በሚፈልጉት ልክ እንዳያስገቡ አድርጓልም ብለዋል፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ማነቆዎችን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አምራች ኢንዱስትሪው ግብርናውን ተከትሎ እንዲያድግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጭ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!