“የሀገር ፍቅር አስተማሪ፣ የነጻነት ፊታውራሪ”

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እልፍ አዕላፍ ልጆቿ ለክብሯ ወድቀውላታል፤ ለፍቅሯ ደምተውላታል፣ ለነጻነቷ ሞተውላታል፡፡ ጠይቃቸው የነፈጓት፣ ፈልጋ የከለከሏት የለም፡፡ ውዱን ስጦታ ሕይወት ሰጥተዋታል፡፡ በሰጧት ሕይዎትም በክብር አኖረዋታል፤ በነጻነት አጽንተዋታል፤ በጠላቶቿ ፊት የማይደፈር ግርማን አላብሰዋታል፡፡ በታሪክ የከበረች፣ የነጻነት ብርሃኗን ያላደበዘዘች አድርገዋታል፡፡

ሀገር በከፋቸው ጊዜ የሚረሷት፣ በጨነቃቸው ጊዜ የሚዘነጓት፣ በየወንዙ የሚዋዋሉባት፣ በየሸንተረሩ ዋጋ የሚቆርጡላት፣ ሰይፍ በተሳለ ጊዜ ይህችንስ አናውቃትም የሚሏት፣ ከጠላት ሰይፍ ለማምለጥ ፈጽመው የሚክዷት፣ በተደሰቱ ጊዜ ደግሞ የሚያስታውሷት፣ በተድላ ዘመን ከፍ ከፍ የሚያደርጓት፣ ጭንቅ በሌለ ዘመን ዘብሽ ነን የሚሏት አይደለችም፡፡

ሀገር ከምንም በላይ የሚወዷት፣ ዋጋ የሚከፍሉላት፣ በጭንቅ ዘመን የሚጸኑላት፣ በመከራ ዘመን ቀድመው የሚቆሙላት፣ ከአንቺ በፊት እኛ እንውደቅ የሚሉላት፣ ሕይወት ገብረው ሠንደቋን የሚያውለበልቡላት፣ እስከ መሰቀያው ድረስ በጽናት የሚከተሏት፣ እስከ መቃብር ድረስ የሚታመኑላት ናት፡፡

እርሳቸው ለፍቅር መሞትን፣ ለሌሎች ነጻነት ተላልፎ መሰጠትን፣ ከራስ በላይ ሌሎችን መውደድን፣ ለእውነት መከራ መቀበልን ሲማሩት፣ ሲያስተምሩት ኖረዋል፡፡ መከራ በመጣ፣ የጭንቅ ቀን በቀረበች ጊዜም የተማሩትን እና ያስተማሩትን በተግባር ፈጽመው፣ ኀያል ፍቅር በትውልድ ልብ ላይ ዘርተው፣ ነጻነትን በፈሰሰች ደማቸው አጽንተው፣ በመከራ የሚጸና ትውልድ ይኖር ዘንድ ቃል ኪዳን ትተው ስለ እውነት አለፉ፡፡

የሀገር ፍቅር አስተማሪ፣ የነጻነት ፊታወራሪ ናቸው፡፡ የጠላት ሰይፍ የማያስደነግጣቸው፣ ጦርና ባሩድ የማያሰጋቸው፣ ሞት የማያስፈራራቸው እውነተኛ ሰው ናቸው ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፡፡ እንደ ዓለት ጠጥረው፣ ከበጎቻቸው ፊት ለፊት ከተኩላዎች ጋር የተዋጉ ታማኝ እረኛ፣ ደግ መልዕክተኛ ናቸው፡፡ ከሞት መልዕክተኛ ጋር ተናንቀዋል፤ በገዳዮቻቸው ፊት በኩራት ቆመዋል፤ ለልባቸው ድንጋጤን ሳያሳዩት፣ ዕውነትን እንዳሉ፣ የሀገራቸውን ስም እንደጠሩ፣ ልጆቻቸውን ስለ ሀገራቸው ፍቅር እና ነጻነት እንዲጸኑ ቃል ኪዳን እያሠሩ አለፉ እንጂ፡፡

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ለማንም ያልተበገረችውን ሀገር ኢትዮጵያን አስገብራለሁ፣ ኢትዮጵያውያንንም እንደ አሻዬ እገዛለሁ፣ ያለችው ጣልያን ተደጋጋሚ የቅኝ ግዛት ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ ታዲያ ባደረገቻቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች እየተሸነፈች፣ ልጆቿን ለኢትዮጵያውያን ጎራዴና ጦር ሲሳይ እየጣለች አፍራ ተመልሳለች፡፡ በአውሮፓ ስልጣኔ ኀያል ከነበሩ ሀገራት መካከል ከግንባር ቀደሞቹ የምትሰለፈው ኢጣልያ በኢትዮጵያ ባደረገቻቸው ተደጋጋሚ የቅኝ ግዛት ሙከራዎች አንገቷን እየደፋች፣ ተንበርክካ እየሰገደች፣ ለጀግኖቹ እጅ እየነሳች በዓለሙ ፊት ሁሉ እያፈረች መመለሷን ታሪክ መዝግቧል፡፡

በሮም ታሪክ ውስጥ ኀይል ዝና ያለው አግውስቶስ ቄሳር አውሮፓን እና አፍሪካን እስያንም ጭምር አስገብሮ በሥልጣኑ ሥር ካደረገ በኋላ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ29 ዓ.ም አይሎስ ጋሎስ በሚባል ጦር አዛዥ የሚመራ እግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ በዚያ ዘመን ገናና መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ የምትበገር አይደለችም፡፡ የባሕር ኀይሏን ጠላት አይሞክረውምና በየብስ መጥቶ የኢትዮጵያን መንግሥት ሊወጋ ገሠገሠ፡፡ ይህን የሰሙ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ከሮም የተላከውን ጦር ከወሰናቸው ማዶ በጀግንነት ወግተው አቆሙት፡፡ ሳይበገሩ ጀግንነታቸውን አሳይተው በሀፍረት ወደ ሀገሩ መለሱት ይላሉ ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በተሰኘው መጻሕፋቸው፡፡

ከጥንት ጀምሮ የነበረው የጣልያን ጠላትነት አልበረደምና በሮም ታሪክ የገነነ ስም ያለው ሌላኛው ንጉሥ ኔሮ የአባቶቹን ደም ለመመለስ ወደ ኢትዮጵያ ጦር ልኮ ድል ኾነ፡፡ ከዘመናት በኋላ እምዬ ምኒልክ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ በነገሡበት ዘመን የቅኝ ግዛት መንፈስ የተጠናወተው የጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን ሊወር የዘመነ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ የተላከው ጦርም በዓድዋ ሰማይ ሥር እንደ ጭስ በኖ፣ እንደ ጉም ተኖ ቀረ፡፡ ጣልያንም ታላቁን ሽንፈት በጥቁሮች ምድር ተሸነፈች፡፡ በኢትዮጵያውያን የመሸነፍ ክብረ ወሰኗንም ከፍ አደረገች፡፡

ከአርባ ዓመታት በኋላም ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኀይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ በነገሡበት ዘመን ጣልያን ለበቀል እና ለወረራ ተመልሳ መጣች፡፡ በዚህም ዘመን አያሌ በደሎችን ፈጸመች፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ከአባቶቻቸው በወረሱት ጀግንነት እና ጽናት ተዋጓት፡፡ ለዓመታት በዘለቀው ጽናታቸውም ድል መቷት፡፡ በዚህ ዘመን በፋሽስት ኢጣልያ ሰማዕትነት የተቀበሉት፣ ኢትዮጵያውያንም አርበኞች በቁጣ እንዲነሱ ያደረጉት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከፍ ብለው ይነሳሉ፡፡

እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ጣልያን ለወረራ በመጣች ጊዜ ከንጉሡ ከግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር በመኾን ወደ ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሀገር ፍቅር እና ክብር በጀግንነት እንዲዋደቁ፣ ነጻነታቸውን እንዲያጠብቁ አበረታተዋል፡፡ በጸሎት ተግተዋል፡፡ ድሉ ጊዜ የሚወስድ ነበርና ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜም ከንጉሡ ጋር አብረው ተመልሰዋል፡፡ አኒህ ታላቅ ጳጳስ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ እንኳን ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያም ለጠላት እንዳትመች፣ ተቆጥታ እንድትነሳ ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ ናቸው፡፡

ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሰሜን ግንባር ከተመለሰ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ፡፡ ከዚያም ኾነው የሰላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ጀመር፡፡ በዚህም ለጣልያን የገቡና በጣልያን አገዛዝ ያመኑ የኢትዮጵያ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ለጣልያን እንዲገቡና በጣልያን ላይ የሚሰብኩትን ስብከት እንዲተው በደብዳቤም በቃልም ይመክሯቸው ጀመር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ግን ማንኛውንም ልመና አልተቀበሉትም ብለው ጽፈዋል፡፡

ታላቁ ጳጳስ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ ከመጣው ፋሽስት ጋር ምንም አይነት ኅብረት አይኖረኝም ብለው እምብኝ አሉ፡፡ ጳውሎስ ፓትሪክ ሮበርትስን ጠቅሰው ሲጽፉ በሐምሌ ወር የኢትዮጵያ አርበኞች ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ለመያዝ ብርቱ ወጊያ አደረጉ፡፡

ኢትዮጵያውያኖች የሚያስገርም እና ከባድ ውጊያም አደረጉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የጣልያን ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያዊያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሱ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ ብለዋል፡፡

ዲያቆን መርሻ አለኸኝ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጻሕፋቸው ደግሞ አርበኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ ከሰላሌ አርበኞች ጋር የነበሩት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ጠላት ከኢትዮጵያውያኑ ነጥቆ ሀገሬ ከተማዬ ብሎ በመቀመጥ በመላ ሀገሪቱ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ የሚመራበትን እና ትዕዛዝ የሚያስተላልፍበትን የአዲስ አበባ ከተማን ትተው ለመሄድ አልፈቀዱም፡፡ በመኾኑም ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ኾኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ፡፡ ካልኾነ ደግሞ እዚህ እሞታለሁ ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ ብለው ጽፈዋል፡፡

ኢኒህ ታላቅ አባት ከጠላት እጅ ወደቁ፡፡ ለፍርድም ቀረቡ፡፡ ይህችም ቀን ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበረች፡፡ ዲያቆን መርሻ የኮርየሬ ዴላሴራ ጋዜጠኛ የነበረውን ፖጃሌን ጠቅሰው ሲጽፉ “አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲኾኑ ጣልያኖች እና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፡፡ ራስዎም አምጸዋል፡፡ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ዳኛም ካህናቱም ኾኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣልያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ኾኑ? ሲል ጠየቃቸው፡፡

አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኀላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬ እና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ አሉ በማለት መዝግበዋል፡፡

ታላቁ ጳጳስ የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው፡፡ አሟሟታቸውም ሕዝብ በተሠበሠበበት በጥይት ተደብድበው እንዲኾን ተደረገ፡፡ ጳውሎስ ዜና ቤተክርስቲያንን ዋቢ አድርገው ሲጽፉ“ አቡነ ጴጥሮስ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው ፋሽስቶች የሀገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣልያ ፋሽስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ይሁን፡፡ የኢትዮጵያም መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን ብለው ተናገሩ” ብለዋል፡፡

እኒህ ታላቅ አባት፣ የአርበኞች አርዓያ፣ ጽኑ ሰማዕት ዛሬም ድረስ በእዝነ ልቡና የሚሰማ ንግግር ተናግረው ለሞት ተዘጋጁ፡፡ ለሀገር ፍቅር እና ለነጻነት ሰማዕትነትን ለመቀበል በጽናት ቆሙ፡፡ በስምንት ካራሚኜሮች ጥይት ተደብድበው ወደቁ፡፡ እንዲህ ተመትተው አልሞቱም ነበር፡፡ አለቃቸው መጥቶ ያቺ መልካም የሚያስቡባትን፣ ፍቅር ያንሰላሰሉባትን፣ ነጻነት የጸነሱባትን አዕምሯቸውን በጥይት ደብድቦ ገደላቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ግን በሞታቸው ገዳያቸውን ጣሉት፡፡ በሞታቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ በቁጣ አስነስተው ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጡት፡፡ ለሀገር ፍቅር መስዋዕትነት መኾን እንደሚያስከብር አስተምረው ሳይኾን መስዋዕት ኾነው አሳይተውታልና ለሀገር ፍቅር መስዋዕት ለመኾን የሚነሳውን አበረቱት፡፡ መሪውን መትተን ተከታዩን አጠፋነው፣ እረኛውን መትተን መንጋውን በተነው ሲሉ ይባስ ብሎ ገንፍሎ ወጣ፡፡ ኢጣልያም እንደ ግብሯ ተሸንፋ ወጣች፡፡

እኒህ ታላቅ አባት ሰማዕትነትን የተቀበሉት ልክ በዛሬዋ ቀን ሐምሌ 22 1928 ዓ.ም ነው፡፡ ስለ ሀገር ለከፈሉት መስዋዕትነት፣ ስለ ክብር ላሳዩት ጽናት ትውልድ እየዘከራቸው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ የሀገር ፍቅርን፣ የሠንደቅ ክብርን ጥግ አሳይተዋልና በታሪክ ሲዘከሩ ይኖራሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደ ሀገር የሚከናወነውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚያግዙ መኾናቸው ተገለጸ።
Next articleምጣኔ ሃብታዊ እድገቱ እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ግብርና የማይተካ ሚና ስላለው ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡