ተስፋ የተጣለበት የሰቆጣ ሴራሚክ ፋብሪካ!

34

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችት ካላቸው አካባቢዎች የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወርቅ፣ ብረት፣ ግራናይት እና ሌሎች ማዕድናት በብዛት እንደሚገኙ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የማዕድን ልማት መምሪያ መረጃ ያሳያል።

በተለይ ደግሞ በአካባቢው ጥራት ያለው ብረት የሚገኝበት በመኾኑ አሁን ላይ በዝቋላ እና ሰሀላ ወረዳዎች ጥናት እየተደረገ ይገኛል። ከጥናት ባለፈ ፋብሪካ ለመገንባት ውል የወሰዱ ድርጅቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የሰቆጣ ሴራሚክ ፋብሪካ አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በ2009 ሥራ ለመጀመር ውል ቢወስድም በጦርነት፣ በኮሮና ወረርሽኝ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት እስከ አሁን ሲጓተት መቆየቱን የሰቆጣ ሴራሚክ ቦርድ ሠብሣቢ ምትኩ በየነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በባለፈው ዓመት ጀምሮ በሰቆጣ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመክፈት የግንባታ ሥራ ቅድመ ዝግጅት እየተሠራ ነው። አሁን ላይም የመጨረሻ ጨረታ ለማውጣት በዝግጅት ላይ መኾኑን ሠብሣቢው ገልጸዋል። አሸናፊውን እስከ ክረምቱ መጨረሻ በመለየት በ2017 ዓ.ም ሸዱን በመገንባት ወደ ማምረት ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፋብሪካው ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ300 በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል ነው ያሉት። ገበያ በማረጋጋት እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል። አካባቢው በማዕድን የበለጸገ በመኾኑ ሌሎች ባለሃብቶችም ገብተው እንዲያለሙ ፈር ቀዳጅ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል። በአካባቢውም ማኅበራዊ ግዴታዎችን ለመወጣት ያግዛል ተብሏል።

በተረፈ ምርቱም ተያያዥ ምርቶችን ለማምረት እና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ፋብሪካው ወደ ሥራ እንዲገባ ማኅበረሰቡ እና የአካባቢው አሥተዳደር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የአማራ ሕንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለፉት ዓመታት በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ሕንጻ እና የመንገድ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የድርጅቱ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ አንስተዋል።

ድርጅቱ የተለያዩ ጥራት ያላቸው ሥራዎችን እያከናወነ ቢገኝም በዋጋ ንረት፣ በኮሮና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን በክልሉ በተፈጠረው ጸጥታ እና አንዳንዶች ደግሞ በዲዛይን ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸው የሰቆጣ የሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ ከ2009 እስከ 2015 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል። በዚህ ዓመት የሰቆጣ ጽሕፈት ቤቱን በመገንባት እና የሰው ኀይል በመመደብ አሸዋ፣ ጠጠር እና የመሳሰሉ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ካፒታል 63 ሚሊዮን ብር መኾኑንም ገልጸዋል። ፋብሪካውን ወደ ሥራ ለማስገባት ጨረታ መውጣቱን የገለጹት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው በአጭር ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ ኾኖ የቆየውን ፕሮጀክት በፍጥነት በመገንባት ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከሰቆጣ ሴራሚክ ማምረቻ በተጨማሪ በምሥራቅ ጎጃም የዞን አሥተዳደር እና የጎጃም የባሕል ማዕከል ግንባታዎች ከተጓተቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። አሁን ላይ የግንባታ ሂደታቸው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ሲኾን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የተፈጠረውን የሰልም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ድርድር ምርጫ ሳይኾን ብቸኛ አማራጭ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ
Next article“በኢትዮጵያ ለተደረገው ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊነት ድጋፍ እናደርጋለን” የአሜሪካ መንግሥት