
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ጀምሯል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቀው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ ክልሉ ያለፈበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ላለፈው አንድ ዓመት የዘለቀው ግጭት የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጎድቶታል ያሉት አፈ ጉባኤዋ የምክር ቤት አባላት ለሰላም ለመሥራት ቀስቃሽ አያስፈልገንም ብለዋል፡፡ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ተገልለው የቆዩበት የሰላም ችግር የመጨረሻ መፍትሔው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደኾነም አመላክተዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ በንግግራቸው ግጭቱ ከፈጠረው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር በክልሉ ሕዝብ ነባር እና ክቡር እሴቶች ላይ ያሳደረው ያልተለመደ ባሕሪ በጊዜ ሊታረም ይገባልም ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ ለሰላም በሚሠሩ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ላይ የተፈጠረው ጥቃት በማኅበረሰቡ ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
ከፖለቲካ የራቁ እና ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ንጹሃን ከሰሞኑ በሰሜን ጎጃም ዞን ገርጨጭ አካባቢ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊትም የክልሉን ሕዝብ ያስቆጣ ነው ብለዋል አፈ ጉባኤዋ በመልእክታቸው፡፡
ጦርነት እና ግጭት መቋጫው ሰላማዊ ውይይት ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ “በክልሉ የተፈጠረውን የሰልም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ድርድር ምርጫ ሳይኾን ብቸኛ አማራጭ ነው” ብለዋል፡፡ የሰላም አማራጭን ባዘገየን ቁጥር የሚፈጠረው ተጨማሪ ቀውስ እና ጉዳት እንደኾነ በመገንዘብ ለሰላም ቀን ከሌሊት መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ ሙስና እና ሌብነትን መታገል እንዲሁም ሕዝብን ለቅሬታ የሚዳርጉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለይቶ ማስተካከል ይገባልም ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ የሚቀለብስ ውይይት እንደምናደርግ ተስፋ አለኝ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!