#ሳምንቱ በታሪክ

28

ያሳለፍነው ሳምንት ጉልህ የታሪክ ክስተቶች ፦

1. ‘አርበኛው’ አቡነ ጴጥሮስ መስዋዕትነትን የተቀበሉበት ልብ ሰባሪ ክስተት ኢትዮጵያዊው የሃይማኖት አባት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፍቼ ከተማ ተወለዱ፡፡ አርበኛው የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ኃይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ወደ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት መጥተውም በዋሸራ የአብነት ትምህርት ቤት የቅኔ ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው በማጠናቀቅ መምህር ኾነዋል፡፡ መምህሩ ወደ ወሎም አቅንተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ያስተምሩ ከነበሩት ሊቅ አካለ ወልድ ጋር ተገናኙ። ሊቁም ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ብሉያትን እና ሐዲሳትን እንዳስጠኗቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

አኝህ ታላቅ ሊቅ (አቡነ ጴጥሮስ) በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመልሰውም ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ መምህር ኾነውም በመሾም ለስድስት ዓመታት አስተምረዋል። ከ1916 ዓ.ም ጀምሮም በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ለሦሥት ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመዛወርም የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህር እና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንስሓ አባት ኾነው የአባትነታቸውን አደራ ተወጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች በጵጵስና እንድትመራ ሲፈቀድላትም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም በጵጵስና ማዕረግ ተሾሙ፡፡

ብፁዕነታቸውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እና ቅድስት ሀገራቸውን በጸሎታቸው እያገለገሉ እና ሕዝባቸውን ደግሞ እያስተማሩ ጠበቁ። በዚህ መልኩ ሀገርን እና ሕዝብን እያገለገሉ ሳሉ አረመኔው የፋሺስት ጣሊያን ጦር በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ጀመረ። በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናት እና መነኮሳትም በፋሽስቱ በግፍ ተገደሉ። ቤተ ክርስቲያናትንም ማቃጠል ተያያዘው። ቅርሶችንም ዘረፈ፡፡

አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመኾን በጸሎታቸው ሊዋጉ ተነሡ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ድረስ ዘመቱ። ፋሺስቱ በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ሲያደርግም እሳቸው ከጓዶቻቸው ጋር ኾነው ፋሽስቱን ተፋለሙት። ወዲህ ደግሞ ለሀገር እና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መኾኑን ሀገሬውን በሚገባ አስተማሩ። በመኾኑም ‹‹የሀገሬ ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በዓደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል›› ብለውም በይፋ ሰበኩ፤ አነሳሱ፤ እርሳቸው ከፊት ኾነው ሕዝቡ “ሆ!” ብሎ እንዲዘምትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበረከቱ።

የጣሊያን ጦርም በየግንባሩ ተሸነፈ። ሴት ወንዱ ጠላትን በሽምቅ ውጊያ አበራየው። የኢትዮጵያ ነጻነትም ልጆቿ በከፈሉት ደም እና አጥንት እንደተከበረ ቀጥሏል። ተንበርካኪው የጣሊያን የጦር መሪዎችም አቡነ ጴጥሮስን ካልገደሉ እረፍት እንደማያገኙ ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ለዚህም ሥውር ወጥመድ አዘጋጁ። እንዳሰቡትም በ1928 ባሳለፍነው ሳምንት ቅዱስ አርበኛው በዓደባባይ መሰዋዕት ኾኑ። “ሞት አይቀርም፤ ስም አይቀበርም” እንዲሉ የአቡነ ጴጥሮስ አኩሪ የአርበኝነት ተጋድሎ እነኾ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲዘከር ይኖራል። በመረጃ ምንጭነት ” ስምዐ ጽድቅ ” መጽሔትን ተጠቅመናል።

2. የመጀመሪያው ባቡር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት መሠረት ያስቀመጡት አጼ ምኒልክ እንደኾኑ በታሪክ ድርሳናት ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። አጼ ምኒልክ በውጭ ሀገር ያስተዋሉትን የባቡር መጓጓዥያ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መጀመሪያ ሀዲድ ያስፈልግ ነበርና ይህንንም የፈረንሳይ መንግሥት እንዲገነባላቸው ጠየቁ። ሁለቱ ሀገራት በነበራቸው ጠንካራ ግንኙነትም የፈረንሳይ መንግሥት የባቡር ሀዲድ ከጅቡቲ ሐረር ድረስ ለመሥራት ይሁንታውን አሳየ። በዚህ መሠረትም የግንባታ ሥራውን በ1890 ዓ.ም ጀመረ። የሀዲድ ግንባታው መነሻውን በቀድሞ አጠራሯ ኦቦክ ከአሁኗ ጅቡቲ አደረገ።

የፈረንሳይ የባቡር ሀዲድ ግንባታ ጠበብቶችም ቀን ማታ ሥራውን ደረጃ በደረጃ አፋጠኑት። የመጀመሪያው ባቡርም ሐምሌ 15 ቀን 1893 ዓ.ም ከጅቡቲ ተነሳ። ከአምስት ሰዓት ጉዞ በኋላ የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ከኾነችው ደወሌ ደረሰ። በዚህ መልኩ የተጀመረው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር 784 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሀዲድ ግንባታ ከሃያ ዓመታት አድካሚ ሥራ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተሠርቶ ተጠናቀቀ። አጼ ምኒልክም “ሰርኪስ” የተሰኘውን ባቡር በ1896 ዓ.ም ገዝተው አስመጡ። ይህ ባቡር በእንፋሎት ኀይል የሚሠራ ነው።

ባቡሩ ሲመጣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከመኳንንቶቻቸው ጋር ድንኳን ውስጥ ከፍ ካለ ሥፍራ ላይ ተቀምጠው ጠበቁት። ባቡሩን ያመጣው ሙሴ ሰርኪስ ባቡሩን ወደፊትም ወደኋላም እያስነዳና የጥሩምባ ድምጹን እያሰማ ኹኔታውን ለአጼው አሳየ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክም ባቡሩ ውስጥ ገብተው ጥቂት ተንሸራሸሩበት።የኾነ ኸኖ የመጀመሪያው ባቡርም ከጅቡቲ ተነስቶ ኢትዮጵያ የደረሰው ሐምሌ 15 ቀን 1893 ዓ.ም ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። በመረጃ ምንጭነት ‹‹የዘመን ታሪክ ትዝታዬ›› መጽሐፍን መጠቀማችንን ልብ ይሏል።

3. የግድቡ መጠናቀቅ ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የገነባችውን የአስዋን ግድብ ያጠናቀቀችው በሐምሌ ወር 1963 ዓ.ም ነበር። ግድቡን ለመገንባት 11 ዓመታት የወሰደ ሲኾን ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይም ወጪ ተደርጎበታል። ግድቡን ለመሥራት ሲታሰብ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ እና እንግሊዝ ቃል ገብተው ነበር። ይሁን እና ሁለቱ ሀገራት ግብጽ ከሶቬየት ኀብረት ጋር የነበራትን ሚስጥራዊ የጦር መሳሪያ ስምምነት እያደር ስለደረሱበት ቃላቸውን አጠፉ።

ሶቬየት ኀብረትም የአሜሪካን እና የእንግሊዝን መሸሽ ተከትላ የአስዋን ግድብ እንዲገነባ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የባለሙያ ድጋፍ አደረገች። የአስዋን ግድብ ለግብጽ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቶላታል። የመጀመሪያው ሀገሪቱ በየዓመቱ ስትቸገርበት የነበረውን ድርቅ አስቀርቶ አረስርሷታል። ሲቀጥልም ግብጽ በክረምት ይገጥማት የነበረውን ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ገትቶላታል።

የግብጽ ግብርና የተመሠረተው ዘመናዊ መስኖ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ የአስዋን ግድብ ዋነኛ የውኃ ምንጭ ኾኖ እያገለገለ ይገኛል። ከግድቡ የሚነሳው የውኃ ኃይል 12 ተርባይነሮችን በማንቀሳቀስ በዓመት 10 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ኃይል በማመንጨት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ሸፍኗል።

የአስዋን ግድብ በመዝናኛ፣ በዓሳ እርባታ እና በሌሎችም ዘርፎች ጭምር ሀገሪቱን እየጠቀማት ይገኛል። ይህ 300 ማይል ርዝመት እና 10 ማይል ስፋት ያለው ግዙፍ ግድብ ተገንብቶ የተጠናቀቀው ባሳለፍነው ሳምንት ሐምሌ 14 ቀን 1963 እንደነበር ቢቢሲ በድረ ገጹ አስታውሷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያን አስመልክቶ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፦
Next articleምሥጋና 🙏