ከ40 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

77

ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከ40ሺ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ጋር ተፈራርሟል፡

ስምምነቱ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሠራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ የገባውን የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን በመጠቀም ለመቅጠር የሚያስችል ነው፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የሥታስቲክስ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ባለፉት ዓመታት በገጠርና በከተማ ግብርና እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት በትክክል ለመለካት የሚያስችል በመኾኑ ለሀገር በቀል ሪፎርም ሥራችን ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

ከ22 ዓመታት በሁዋላ በሚሰበሰበው በዚህ ሥራ መረጃውን የሚያሰባስቡ ዜጎች ምልመላና ቅጥር በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሠራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ በገባው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (ELMIS) አማካኝነት እንዲፈጸም ለማስቻል ስምምነቱ መደረጉን ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡

ይህም ፍትሐዊ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በኾነ መልኩ የቅጥር ሂደቱን በማጠናቀቅ በፍጥነት ሥራውን ለማስጀመር እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በመላ ሀገሪቱ የሚተገበርና መረጃዎችን በአጭር ጊዜና በጥራት ለማሰባሰብ የሚያስችል መኾኑ የሥታስቲክስ አገልግሎቱ ለሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ በላቀ ደረጃ ተመራጭ እንዳደረገው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡

በመረጃ ማሰባሰብ ሥራው ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በየአካባቢያቸው በሚገኙ የሥራ ዕድል ጽሕፈት ቤት በመገኘት የባዮሜትሪክ መረጃቸውን በመስጠት መመዝገብና በሥራው ላይ መሰማራት እንደሚችሉም በስምምነቱ ወቅት መገለጹን ኢቢሲ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 5 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት የተለያዩ የክልከላ ውሳኔዎችን ማሳለፋን አስታወቀ።