
ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በተከሰተ የኮሌራ በሽታ 4ሺህ 983 ሰዎች ለህመም እንደተዳረጉ በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ ገልጸዋል፡፡
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ሐምሌ ወር መጀመሪያ ድረስ የኮሌራ በሽታ ተከስቶ እንደማያውቅ አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡
ከሐምሌ 8/2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በ16 ዞኖች እና 58 ወረዳዎች ላይ ብዛት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚሠባሠቡባቸው ቦታዎች ሰዎች ለህመም እና ለህልፈት እንደተዳረጉም ተናግረዋል፡፡
አቶ አብርሃም ከታኅሣሥ/2016 ዓ.ም ጀምሮ በተገለጹት ዞን እና ወረዳዎች በሽታውን መቆጣጠር እንደተቻለ ነው ያብራሩት፡፡
አሁን ላይ በባቲ ወረዳ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በስፋት ተሰራጭቶ በምሥራቁ የክልሉ ክፍል እንደተስፋፋ እና ወደ ምዕራቡ ክፍል ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና አካባቢያቸው ባሉ ቦታዎችም እንደተከሰተ ነው የገለጹት፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ ለጤና ባለሙያዎች እና ለሚመለከታቸው አጋር አካላት ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡
በሽታው በዋናነት በተበከለ ውኃ እና ምግብ፣ ከህመምተኛ ወደ ጤነኛ ሰው በንክኪ እንደሚተላለፍም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አቶ አብርሃም ኅብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ፣ ንጽህናው የተጠበቀ ውኃን በመጠቀም እና ምግብን አብስሎ በመመገብ በሽታውን መከላከል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
ከክረምት ጋር ተያይዞ ጎርፍ በስፋት ስለሚኖር ምንጮች የመበከል ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ውኃን አክሞ እና አፍልቶ በመጠቀም በሽታውን በቀላሉ መከላከል እና መቆጣጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የበሽታው ምልክቶች ከታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የባለሙያ ድጋፍ እና የህክምና አገልግሎት ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት ባይኖሩ እና ለሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ማድረስ ባይቻል በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነጻ የስልክ መስመር 6981 በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻልም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!