
ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከስድስት ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ሠራዊቱ በቀበሌው በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ዜጎች ያዘጋጀውን የእለት ደራሽ ድጋፍ ዛሬ ለዞኑ አስተዳደር አስረክቧል። ድጋፉን ለጎፋ ዞን ያስረከቡት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ የደረሰው ድንገተኛ አደጋ ባስከተለው ጉዳት ማዘናቸውን ገልፀዋል። የእለት ደራሽ ድጋፉ የስንዴ ዱቄት፣ ብስኩት፣ ስኳር፣ እንዲሁም አንሶላና ብርድልብስ ማካተቱን ገልጸው ድጋፉ ስድስት ሚሊዮን 305 ሺህ ብር እንደሚገመት ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርጉ አካላትን ያካተተ ቡድን በመላክ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በዛሬው እለትም የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሠራዊቱ ለወገን ያለውን አለኝታነት ዳግም ማረጋገጡን ገልፀው፣ ለተደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!