
ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎርፍ አደጋ ስጋቱን ለመከላከል እና ለመቀነስ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት ሥራ ጥሩ የሚባል መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ተናግረዋል፡፡
ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀውን ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ከጎርፍ አደጋ ሥጋትነት ወደ ዕድል ለመቀየር ከክልል እስከ ቀበሌ በቅንጅት እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
በተያዘው የክረምት ወራት ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀውን ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ሁኔታ ተከትሎ በጣና ሐይቅ ተፋሰስ አዋሳኝ አካባቢ ባሉ ሦስት የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት ተፈጥሯል፡፡
ትንበያውን ተከትሎም የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ አደጋውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ቀደም ብሎ መጀመሩም ተገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት በክረምት ወራት የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው በያዝነው ዓመት በሚፈለገው ልክ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ነው ያሉት፡፡
ዞኑ የገጠመውን የሰላም እጦት ታሳቢ በማድረግ የጎርፍ አደጋ ስጋቱን ለመቀልበስ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት የሚያሥመሠግን ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ በሚገኙ ደራ፣ ፎገራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች በሚገኙ 21 ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በሊቦ ከምከም ስምንት ኪሎ ሜትር፣ በደራ 22 ኪሎ ሜትር እና በፎገራ ወረዳ አንድ ኪሎ ሜትር የጎርፍ መከላከያ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
በርብ እና ጉማራ ወንዞች መካከል በሚገኘው የፎገራ ወረዳ ተጨማሪ የጎርፍ መከላከያ ሥራ ይፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
በሦስቱ ወረዳዎች ውስጥ በተለዩ 21 ቀበሌዎች የሚኖሩ 56 ሺህ 200 የማኅበረሰብ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ ስጋቱ ቀጥተኛ ተጠቂዎች ሊኾኑ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ጥላሁን ደጀኔ በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በእንስሳት እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አፈጻጸም እና ተግባራዊ ምላሽ በሚመለከትም ከቢሮው ጋር በቅርበት እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
እንደ ዋና አሥተዳዳሪው ገለጻ የቅድመ ዝግጅት ሥራው የአየር ትንበያውን በጥልቀት መገምገም፣ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት፣ የአደጋ ስጋት ምላሽ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ሃብት ማሠባሠብ እና ግብዓቶችን ማቅረብ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ያዘጋጀውን እና ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ቁሳቁስ ወረዳዎች ተረክበዋል ብለዋል፡፡
ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዲስ አይደለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው መጠነኛ ድጋፍ እና እገዛ ከተደረገላቸው ስጋቱን ወደ ዕድል የመቀየር አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
የክልሉ ውኃ እና ኢርጂ ቢሮ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በጥናት ላይ ተመሥርቶ በዘላቂነት ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ጊዜያዊ መፍትሔ በማፈላለግ በኩል የሚያደርገው ጥረት አበረታች ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች ተቋማትም ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰበውን ችግር ለመከላከል የጋራ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!