ከስሀላ ሰየምት ወደ ዝቋላ በጀልባ ተሳፍረው ሲጎዙ የነበሩ 19 ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል የስሃላ ሰየምት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሲሳይ ብሩ ገለጹ።

64

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትናንት ከቀኑ 6፡00 ገዳማ ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጎዙ ከነበሩት በግምት 26 ሰዎች ውስጥ 19 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የስሃላ ሰየምት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሲሳይ ብሩ ገልጸዋል።

ከ26ቱ ሰዎች አንድ ሕጻንን ጨምሮ 7 ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕይወታቸው ተርፏል ያሉት አቶ ሲሳይ የሟቾቹን ቁጥር ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸዋል። አደጋው ከደረሰ በኋላ የሟቾችን አስከሬን ለመፈለግ በተደረገው ጥረት እስከ ዛሬ ድረስ ሁለት ሰዎች ብቻ አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል። ዋና አሥተዳዳሪው እንደገለጹት ሕይወቱ የተረፈው አንድ ሕጻን ከፍተኛ ጉዳት ስላስተናገደ ወደ ሰቆጣ ተፈራ ኃይሉ መታሰብያ ጠቅላላ ሆስፒታል ሲላክ የተቀሩት ስድስቱ መሸሀ ጤና ጣብያ ገብተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

ከአራት ዓመታት በላይ ከጥቅም ውጭ ኾኖ የቆየው እና እስከ ሰኔ ወር መጨረሻዎች ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ከስሃላ – ዝቋላ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁ የሰው ሕይወት መቅጠፉን እንዲቀጥል ምክንያት መኾኑን አቶ ሲሳይ ለአሚኮ ተናግረዋል። አሚኮ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ወዳጆችና ዘመዶች መጽናናትን ይመኛል።

ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎቹን አስመረቀ፡፡
Next articleበሦስት ወረዳዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋት መኖሩን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታወቀ፡፡