
ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲያስለጥናቸው የነበሩ 1 ሺህ 10 ተማሪዎቹን ዛሬ አስመርቋል፡፡
ኮሌጁ 217 ተማሪዎቹን በዲግሪ ሲያስመርቅ ቀሪዎቹን ደግሞ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት ነው ያስመረቀው፡፡
ኮሌጁ ሀገሪቱም ይሁን ክልሉ ያሉባቸውን የተማረ የሰው ኀይል ክፍተት በመሙላት ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሥራ ፈላጊ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ትውልድ በመፍጠር የማይናቅ አበርክቶን እየተወጣ እንደኾነ የገለጸው ኮሌጁ ዛሬም የተመረቁ ተማሪዎች ከሥራ ጠባቂነት የተላቀቁ እና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎችም የሚተርፉ ስለመኾናቸው ነው የተብራራው፡፡
በተማሪዎች ምረቃ ላይ የተገኙት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ብለዋል፡፡
ሰላም ከሌለ ትምህርትም ኾነ ሥራ ፈጥሮ ራስንም ወገንንም መጥቀም አይቻልም ያሉት ኀላፊዋ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ነው ያሳሰቡት፡፡
መምሪያ ኀላፊዋ ተማሪዎች ሥራ ጠባቂ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ በመኾን ከራሳቸው አልፈው ሀገር የሚያስጠራ ሥራ እንዲሠሩ ተቀርጸው የወጡ ስለመኾናቸው አንጠራጠርም ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹም ባገኙት ዕውቀት ከራሳቸው አልፈው ለወንድም እህቶቻቸው ሥራ ለመፍጠር እንዲተጉም አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎች የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ ሁሌም ለሰላም የሚተጉ እና ተሳስተው ባልተፈለገ የጥፋት ጎዳና የሄዱ ወንድሞቻቸውን እንዲመልሱም አሳስበዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩት ትምህርት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም እንደሚተርፉ ነው የተናገሩት፡፡
ሰላም ከሌለ ያሰቡትን ማሳካት እንደማይችሉ የሚገልጹት ተመራቂ ተማሪዎቹ በቀያቸው ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው ያስረዱት፡፡
በተሳሳተ እሳቤ ውስጥ ገብተው ራሳቸውንም ይሁን ወገናቸውን እየጎዱ ያሉ ወንድም እህቶቻቸውን ለመመለስ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!