
አዲስ አበባ: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የ2016 ዓ.ም የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት የመስክ የሠራተኞች ሥልጠና የመዝጊያ ፕሮግራም አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ.ር) በማጠቃለያ ፕሮግራሙ የሁለት ወር ሥልጠና የተሰጠው የሀገሪቱን የኅብረተሰብ ጤና መረጃ ጥራት ባለው መልኩ እና ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ ተሠብሥቦ አስፈላጊ መረጃዎች ማግኘት እንዲቻል ነው ብለዋል።
የዩኤስ ኤይድ ተወካይ ጆናታን ሮስ ሥልጠናው የጤና ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
ጥራት ያላቸው መረጃዎችን በመሠብሠብ ብዙ ሕዝባዊ የጤና ሁነቶችን በመረጃ ተደግፎ ለመሥራት ያግዛል፤ በዚህም ዩኤስኤይድ ድጋፍ እንዲያደርግ አሳማኝ ምክንያት ኾኖ አግኝቶታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ የጤና መረጃው ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትርጉም ያለው በመኾኑ የተወሳሰቡ መረጃዎችን እንዴት መሠብሠብ እንደሚቻል መታወቁ ወሳኝ ነው ብለዋል።
መረጃው ለጤና ሥርዓት ግንባታ፣ ለፖሊሲ ቀረፃ፣ ለጤና ደኅንነት ግንባታ እና ሌሎች ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማቅረብ የሚጠቅም መኾኑን አንስተዋል።
ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 450 ባለሙያዎች ለሁለት ወራት ሠልጥነው የመስክ እና የናሙና ሙከራዎችን ጨምሮ ሥልጠናውን ዛሬ አጠናቅቀዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!