
ጎንደር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ ሥስተዳደር ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን፣ ልማትን እናስቀጥላለን፤ በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የከተማ አሥተዳደሩ አስታወቋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ በዛሬው እለት የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና መንግሥት በጎንደር ከተማ እያከናወናቸው ስለሚገኙ የልማት ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት ያለመ እንደነበር ተናግረዋል።
ሕዝቡ በከተማዋ ለተጀመሩ የልማት ሥራዎች ድጋፉን ለማሳየት የተካሄደ ሰልፍ መኾኑን ያነሱት አቶ ባዩህ የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት፣ ከአዘዞ እስከ አርበኞች አደባባይ የአስፋልት መንገድ ሥራ እንዲሁም በከተማዋ ያለው የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግርን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የፋሲል አብያተ መንግሥታት ታሪካዊ የጥገና ሥራ፣ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ተግባራት እየተከወኑ መኾኑንም ገልፀዋል።
አቶ ባዩህ የከተማዋ ነዋሪዎችም የልማት ሥራዎችን በተለያዩ መድረኮች ድጋፋቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን አንስተው ዛሬም ለሰላም እና ለልማት ያለውን ድጋፍ የሚገልጽ ሰልፍ በስኬት ማካሄዳቸውን አስታውቀዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ለተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት እና የፖለቲካ አመራሮች ሰልፉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት አስተዋፅኦም አመስግነዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!