
ጎንደር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ ለመንግሥት የልማት ሥራዎች ዕውቅና የሚሰጥ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በፋሲለደስ ስታዲየም ተካሂዷል። በሕዝባዊ ሰልፉ የከተማዋ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ሕዝባዊ ሰልፉ መንግሥት በጎንደር ከተማ እያከናወናቸው ስለሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚደግፍ፣ ለመንግሥት ዕውቅና በመስጠት ምሥጋና ለማቅረብ ያለመ ነው።
በድጋፍ ሰልፉ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መንግሥት እየከናወናቸው ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚበረታታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለልማቱ ያላቸውን ድጋፍም አረጋግጠዋል።
ከልማት ሥራው ጎን ለጎን የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ማኅበረሰቡ ለሰላም የራሱን ተሳትፎ ማበርከት ይገባዋል ብለዋል። ነዋሪዎቹ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁም ጠይቀዋል።
በተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዮህ አቡሀይ ለውጡን ለመቀልበስ በሚሠሩ አካላት የተፈጠሩ ጊዜያዊ ግጭቶች፣ አሉባልታዎች እና መፈናቅሎች ሳይበግሩን ለውጡን ማጽናት እና የለውጡ ቱሩፋት ተቋዳሽ መኾን ይገባል ብለዋል።
የመላው አማራ ሕዝብ እና የጎንደር ከተማ ነዋሪ ጥያቄዎች የመንግሥትም ኾነ የብልጽግና ፓርቲ ጉዳዮች ኾነው ምላሽ እንዲያገኙ ሰፊ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉት በሰላማዊ እና ሕጋዊ አግባብ ብቻ መኾኑን መንግሥት ያምናል ነው ያሉት፡፡
በጦርነት ቀጣይነት ያለው መፍትሔ ማምጣት አይቻልም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መፍትሔው ድርድር እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ማክበር መኾኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ በዓለም ባንክ፣ በክልሉ እና በከተማው የመቀናጆ በጀት በ2 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር የተገነቡ ዋና ዋና የመሠረተ ልማቶች፣ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ቄራ እና ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ እንደሚገኙም አሳውቀዋል።
ጎንደርን አቋርጠው በሚያልፋ የቀሀ፣ የሽንታ እና የድማዛ ወንዞች ላይ ዘጠኝ የመካከለኛ ድልድዮች፣ ስምንት የድልድይ አገናኝ መንገድ፣ ስድስት የወጣቶች መዝናኛ ፖርኮች፣ 33 ነጥብ 15 ኪሎ ሜትር የውኃ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ እና 85 ነጥብ 28 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ባዩህ 129 ነጥብ 86 ኪሎ ሜትር የመብራት ማስፋፊያ ሥራዎች የተሠሩ መኾኑን ገልጸው በቀጣይም ትልልቅ እና የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያሳልጡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ነው ያብራሩት፡፡
ኅብረተሰቡ ለልማቱ 233 ሚሊዮን 370 ሺህ 705 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በጉልበቱ በማዋጣት ለፕሮጀክት ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የመገጭ ግድብ የነበሩበት ችግር ተቀርፈው እና ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት ወደ ሥራ መገባቱን አስገንዝበዋል፡፡
ግድቡ ከመስኖ ሥራ ባሻገር የጎንደር ከተማ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የኾነውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ታሳቢ ተደርጎ በመሠራት ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ከአዘዞ አርበኞች አደባባይ የአስፖልት ሥራን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ የኾነው የኮሪደር ልማት በመሐል ከተማዋ ፒያሳ ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
አቶ ባዩህ የፋሲል አብያተ መንግሥታት ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በከፍተኛ በጀት የጥገና ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ጥገናው አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚወስድ ሲኾን ከጥገናው ባሻገር ለጎብኝዎች ምቹ አገልግሎት እንዲሰጥ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት።
ጎንደር ከተማ ከመቼውም ጊዜ በላይ የፌዴራል መንግሥቱ ትኩረት አግኝታ የከተማዋ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎች እና መሠረታዊ የከተማዋን ችግሮች ለመፍታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለከተማው የለውጥ ሂደት የግንባር ቀደምትነት ሚና ያላቸውን ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ን አመሥግነዋል።
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!