
አዲስ አበባ: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ እና እየተደረገ ባለው ድጋፍ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ አካባቢው ላይ በመገኘት ተጎጂዎችን ማጽናናታቸውን ገልጸዋል።
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ሃዘናቸውን እና አጋርነታቸውን ሲያሳዩ መቆየታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ድኤታዋ የተባበሩት አረብ ኢሜሬት ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚውል 75 ቶን ምግብነክ እና ሌሎች ድጋፎችን ወደ ኢትዮጵያ ዛሬ ማለዳ መላኳን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ የሟቾች ቁጥር 231 ደርሷል ብለዋል ሚኒስትር ድኤታዋ በመግለጫቸው። አሁንም የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሰላማዊት ካሳ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በዞኑ ስጋት ያለባቸው 14 ሺህ ዜጎች ተለይተው በአራት የጊዜያዊ መልሶ ማቋቋሚያ ስፍራዎች እንዲገቡ በጥናት መለየቱም ተመላክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚኾን የሃዘን ቀን ማወጁን ያስታወሱት ሚኒስትር ድኤታዋ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ ዓለማት ባሉ ኤምባሲዎች የሀገሪቱ ሰንደቅዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ነው ያሉት።
መንግሥት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ብሔራዊ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ ነውም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!