
ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኮሌጁ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛ እና በማታው መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን 409 ተማሪዎች ነው ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስመረቀው። ከተመራቂዎች ውስጥ 150ዎቹ ሴቶች ናቸው።
የብርሃን ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር የዓለምሰላም ወርቁ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ኮሌጁ መማር ለሚፈልጉ ወገኖች በተለያዩ ሙያዎች ዕድሉን እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በ4ኛው ዙር የሥልጠና መርሐ ግብር ለ52 ተመራቂዎች በነፃ እና በከፊል ክፍያ ዕድሉን አመቻችቶ ተጠቃሚ እንዲኾኑ አስችሏል ብለዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የአንድ ሀገር ዕድገት የሚረጋገጠው በመንግሥት ብቻ ሳይኾን በግሉ ሴክተር በሚሠራ የልማት ሥራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የግሉ ሴክተር ማኅበራዊ ተቋማትን ሲደግፍ ውጤት እንደሚመጣም ነው ያስገነዘቡት።
ሀገርን ለማልማት ብርሃን ኮሌጅ የራሱን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደኾነም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ኮሌጁ በጥናት እና ምርምር የተደገፈ ችግር ፈቺ ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በአራተኛ ዙር በኮሌጁ የተመረቁ ተማሪዎች 315 በሁለተኛ ዲግሪ እና 94 በመጀመሪያ ዲግሪ መኾናቸውን ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!