የሕዝብን ጥያቄ በማድመጥ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

52

ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ ለመንግሥት የልማት ሥራዎች ዕውቅና የሚሰጥ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በፋሲለደስ ስታዲየም እየተካሄደ ነው። በሕዝባዊ ሰልፉ የከተማዋ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ሕዝባዊ ሰልፉ መንግሥት በጎንደር ከተማ እያከናወናቸው ስለሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚደግፍ፣ ለመንግሥት ዕውቅና በመስጠት ምሥጋና ለማቅረብ ያለመ ነው ተብሏል።

የፌዴራል መንግሥት ለከተማዋ ልማት ትኩረት በመስጠት ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመሩ ነዋሪዎቹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

የጎንደር እና አካባቢውን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መኾኑን ነዋሪዎቹ ባካሄዱት ሰልፍ አረጋግጠዋል፡፡

ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን፤ የተጀማመሩ የልማት ሥራዎችን እናስቀጥላለን፤ የሕዝብን ጥያቄ በማድመጥ ችግሮች በውይይት እና በድርድር ለመፍታት መንግሥት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደግፋለን ሲሉ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በጎንደር ከተማ የአጼ ፋሲል ቤተመንግሥት እድሳት፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የመንገድ ግንባታ፣ የውኃ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ከጎንደር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአይከል ከተማ አሥተዳደር እና በሁለቱ የጭልጋ ወረዳዎች በተካሄደ ሕዝባዊ ውይይት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም አረጋገጠ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመሬት መደርመስ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን አጽናኑ።