በአይከል ከተማ አሥተዳደር እና በሁለቱ የጭልጋ ወረዳዎች በተካሄደ ሕዝባዊ ውይይት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም አረጋገጠ።

28

ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአይከል ከተማ አሥተዳደር እና በሁለቱ የጭልጋ ወረዳዎች ያሉ የሰላም እና የፖለቲካ መልካም ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ስጋቶች እና ከስጋት መወጫ መንገዶች በሚል በተዘጋጀ ሰነድ ዙሪያ በአይከል ከተማ አሥተዳደር በስምንቱ ቀጣናዎች ጠቅላላ የሕዝብ ውይይት ተካሂዷል።

የክልሉን ብሎም የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ትኩረት ያደረገ ውይይት ነው የሁለቱ ጭልጋ ወረዳ መሪዎች በተገኙበት የተካሄደው።

በውይይቱም ከተማዋ በዞኖቹ ከሚገኙ ወረዳዎች የተሻለ ሰላም ያለባት፤ ብሎም ለዞኑ ጭምር ደጀን የኾነበት የሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ተግባብቶ ያለበት መኾኑ በውይይቱ ተነስቷል።

የመድረኩ መሪዎች ሕዝቡ ሰላም እና ልማት ፈላጊ፤ ከመንግሥት ጎን በመኾን ከሌሎች ወንድም እና እህት ሕዝቦች ጋር በሰላም መኖር የሚፈልግ መኾኑን የእስካሁን ቆይታው ያሳያል ብለዋል።

አንዳንድ ግለሰቦች የጠላትን ሃሳብ እና ተግባር ባለመረዳት ብሎም በሐሰተኛ የጠላት ትንታኔ በመታለል ከሚሄዱበት የጥፋት መንገድ እንዲመለሱ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ቀጣናውን ብሎም ከተማውን ሰላም ለመንሳት ኾን ብለው ለጠላት የሚሠሩ አካላትን ለማስተማር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በውይይቱ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሸማግሌዎች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሕግ የበላይነት እንዲከበር ከመንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ካውንስሉ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነትን ሳያስተናግድ ሁለቱ ወገኖች ወደሰላም እንዲመጡ ይሠራል” የሰለም ካውንስሉ ዋና ሰብሳቢ ቆሞስ አባ ዩሴፍ ደስታ
Next articleየሕዝብን ጥያቄ በማድመጥ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡