
ባሕር ዳር: ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራችን ኢትዮጵያ በየጊዜው የገጠሟትን ፈተናዎች በሕዝቦቿ ትብብርና አንድነት በከፍተኛ ድል አድራጊነት መንፈስ ድል እያደረገች የተሻገረች ሀገር መኾኗን በኮንፈረሱ የሰላም ካውንስሉ ዋና ጸሐፊ ፓስተር አማን ሷልህ ተናግረዋል።
በክልሉ የተፈጠረው ችግር ለበርካታ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምስቅልቅሎች ዳርጎናል ብለዋል።
የክልሉን ሰላም ለመመለስና እንደቀደመ ታሪኩ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል የሰላም ካውንስሉን ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ በማቋቋም የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድና መፍትሔ ሀሳቦች ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
ፓስተር አማን እንደገለፁትም በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱ ወገኖች ባመኑበት አካል አማካኝነት ችግራቸውን በውይይትና በድርድር ብቻ እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የካውንስሉ ዋና አላማ እንደኾነ አንስተዋል።
የሰለም ካውንስሉ ዋና ሰብሳቢ ቆሞስ አባ ዩሴፍ ደስታ የሰላም ካውንስሉ ሁለቱ ወገኖች እያለቀ ያለውን ንፁሀንና እየተጎዳ ያለውን ኅብረተሰብ ግምት ውስጥ አስገብተውና ተኩስ ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል።
ያመኑበትን አደራዳሪ መርጠው እንዲነጋገሩ እና እንዲደራደሩ ካውንስሉ ያመቻቻል ብለዋል ዋና ሰብሳቢው። ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ፣ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነትን ሳያስተናግድና በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ይሠራል ነው ያሉት።
ካውንስሉ እንደአስፈላጊነቱ ለሰላሙ መምጣት ያግዛሉ ያላቸውን ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሲቪክ ማኅበራትና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ጋር እንደሚሠራና ከሁለቱ ወገኖች የሚሰጠውን ምላሽ በየጊዜው ለሕዝብ ግልፅ እያደረገ እንደሚሄድ በመድረኩ ተገልጿል።
በመድረኩ ተሳታፊዎች በሁለቱ ወገኖች የሚከናወን ድርድር እና ውይይት ምን መምሰል አለበት በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳቦች በስፋት ተነስተዋል። በመድረኩ አወያዩችም ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በኮንፈረንሱ ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎችና ከጎንደር ከተማ ክፍለ ከተሞች የመጡ አካላት፣ የሰላም ካውንስል አባላት እና ሌሎች አጋር አካላት መሳተፋቸውን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!