
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተዘጋጀውን ዐውደ ጥናት ተካፍለናል ብለዋል፡፡ ዐውደጥናቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት እና በቢግ ዳታ፣ ጄኔሬቲቭ ኤ.አይ፣ በአመራሮች ውሳኔ አሰጣጥ፣ በፖሊሲ እና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ውጤታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ የተወሰደበት ነበር ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዛሬ ላይ በሁሉም መስኮች አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው፡፡ በመንግሥት አሠራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ሌሎችም መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ እኛም በዚህ ዘርፍ በርትተን በመሥራት እና የሕዝባችንን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በማበልፀግ መጠቀም ይገባናል ብለዋል፡፡
“የቴክኖሎጂውን ሙሉ አቅም ተገንዝቦ ወደተግባር የሚለውጥ የሰው ኃይል መገንባት ደግሞ ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ዐውደ ጥናቶች ጉልህ ሚና እንዳለቸው እናምናለን፡” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ።
በወዳጅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ባደረገው ፕሪሳይት በተባለው ተቋም ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ጥናት በዘርፉ ያቀድነውን ወደመሬት ለማውረድ ከሚሰጠው አቅጣጫ አንጻር ስኬታማ ነበር ብለዋል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልእክት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!