ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የጎርፍ አደጋ ስጋት ላለባቸው የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች ድጋፍ አደረገ፡፡

33

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የውኃ ማከሚያ ኬሚካል እና ቁሳቁስ የጎርፍ አደጋ ስጋት ላለባቸው የደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ሁልጊዜም በየዓመቱ ክረምት በገባ ቁጥር የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው የፎገራ፣ የደራ እና የሊቦ ከምከም ወረዳ ነዋሪዎች በተያዘው ክረምትም የጎርፍ አደጋ ስጋት አለባቸው ተብሏል፡፡

የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ድርጅት ትንበያን ተከትሎ በአካባቢው ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመቀነስ እና ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ የቅድመ ዝግጅቱ አንድ አካል የኾነው የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ከሦስቱ ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትም በወረዳዎቹ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚሰጋውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ካደረጋቸው ቅድመ ዝግጅቶች መካከል የተለያዩ ውይይቶችን ማድረግ፣ በጀት መመደብ እና ቁሳቁስ ማቅረብ እንደኾነ ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል፡፡

ዛሬም ለወረዳዎቹ ከተሠጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መጠናቀቅ በኋላ ድጋፉን ለሦስቱ ወረዳዎች ስለማስረከባቸው አብራርተዋል፡፡ የውኃ ማከሚያ ኬሚካል፣ ባለ10 ሺህ ሊትር ሮቶዎች፣ 1 ሺህ የውኃ ጀሪካን፣ 398 ሺህ ሳሙና ለወረዳዎቹ ድጋፍ የተደረገ ሲኾን የሚከሰትን አደጋ ለመከላከል ሁለት ቦቲ መኪኖች ዝግጁ ኾነዋል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለሦስቱ ወረዳዎች ያደረገው የውኃ ማከሚያ ኬሚካል እና ቁሳቁስ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መኾኑን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን ታወጀ።
Next article“የሕዝባችንን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በማበልፀግ መጠቀም ይገባናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ