
ከሚሴ: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች ከክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጎን ለጎን የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ አሳስበዋል። በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እንሠራለን ብለዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰለሞን ይትባረክ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 ዘርፎች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከ 4 መቶ ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ያሉት ኀላፊው። በዚህ ተግባርም ከ 1 መቶ 40ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ከማውጣት ለማትረፍ ታቅዷል ነው ያሉት። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች የአረጋዊያንን ቤት ከመጠገን ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ከመከወን ጎን ለጎን የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ወጣቶች በበኩላቸው በመርሐ ግብሩ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው ሁሉም አካል በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ሊሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!