
አዲስ አበባ: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው አራተኛው ዓለም አቀፍ “ፋይናንስ ለልማት” ጉባኤ ተጠናቅቋል። ዓለም አቀፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ማዕከል አድርጎ በአዲስ አበባ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የመጀመሪያ ክፍል በስኬት ተጠናቅቋል።
የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ የገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መግለጫ ሰጥተዋል። የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በመግለጫው “ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የአረንጓዴ አሻራ ሥራን ተቋማዊ አድርጋ እየሠራች በመኾኑ በጥረቷ ልክ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል” ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ጉባኤው ታዳጊ ሀገራት በተለይም አፍሪካዊያን ድምፃቸውን ያሰሙበት ስኬታማ ጉባኤ እንደነበርም አስረድተዋል። አራተኛው ዓለም አቀፍ “ፋይናንስ ለልማት” ጉባኤ የኢትዮጵያን አቅም እና የልማት መነቃቃት በማሳየት ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ትርፍ የተገኘበት ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ናቸው።
በተመድ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ ጁንዋ ሊ ተመድ በታዳጊ ሀገራት የሚነሱ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የውስጥ ገቢን ማሳደግ ላይ እንዲሠሩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ተመድ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ፍሰት እንዲስተካከል ይሠራልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የተካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት የዝግጅት ጉባኤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2025 በስፔን ለሚካሄደው ዋና ጉባኤ ትልቅ ግብዓት የተገኘበት ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!