ችግሮችን በመቋቋም የፍርድ ሂደቶችን ለማሳለጥ እየሠራሁ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

6

ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመዛግብት ዕድሜን ከስድስት ወር እንዳይበልጥ እና የፍርድ ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት መደረጉን የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ በወረዳ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡት ከ41 ሺህ በላይ መዝገቦች መካከል 99 በመቶ የሚኾኑት ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ያገኘናቸው ተገልጋዮችም ባገኙት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚደርስባቸው እንግልት እንደቀረላቸው ነግረውናል፡፡ የፍርድ ጥራትን ከማስጠበቅ አንጻርም በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ የወረዳ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ጥራት በአማካኝ ሲታይ 59 በመቶ መድረሱን አንስተዋል፡፡

በዞኑ በመደበኛ ፍርድ ቤት የተሻለ አገልግሎት መስጠት ቢቻልም ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር አንጻር በተዘዋዋሪ ችሎት የተሰጠው አገልግሎት ግን ዝቅተኛ መኾኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ከ3 ሺህ 700 በላይ መዝገቦች ቀርበው ለ3 ሺህ 350 መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ለባለ ድረሻ አካላት ችግሮችን የለየ የሕግ ውይይት እና ሥልጠናዎች እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በሶማሊያ መንግሥት የሚሰጡ የትንኮሳ መግለጫዎችን በቅርበት እየተከታተለች ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next article“ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ በሠራችው ልክ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል” የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ