
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የሶማሊያ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የትንኮሳ መግለጫዎች ኢትዮጵያ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት ከሚያቀርባቸው መሰረተ ቢስ ክሶች በተቃራኒ ኢትዮጵያ ወንድም ለሆነው የሶማሊያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከሦስት አሥርት ዓመታት ለበለጠ ጊዜ መሥዋዕትነት እየከፈለች እንደምትገኝ አመላክቷል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መልሶ ግንባታ የከፈለችውን ዋጋ በዘነጉ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እየተሰነዘረባት ባለው በርካታ ኀላፊነት የጎደለው ክስ ማዘኗን መግለጫው አንስቷል፡፡ በመሆኑም ለቀጣናዊ ነፃነት፣ ባሕላዊ ትስስር፣ በደምና በላብ የተገነባውን ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት በማስገባትም ኢትዮጵያ ለተሰነዘሩባት መሠረተቢስ ክሶች ምላሽ መስጠትን እንዳልመረጠች አመልክቷል፡፡
ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያ ለሀገራቱ ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ትዕግስትንና አዎንታዊ ተሳትፎን አማራጭ ማድረጓን ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሚደረጉ ሕገወጥ የቀላል ጦር መሳሪያዎች ዝውውር ጉዳይ በጥልቀት እንደሚያሳስባት ሊሰመርበት እንደሚገባም መግለጫው አስገንዝቧል፡፡
ቀጣናው በግጭቶች፣ በማይፈተሹ የጠረፍ መስመሮች እንዲሁም በድንበር የደኅንነት ችግሮች እየታመሰ በመኾኑ የቀጣናው ሀገራት እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን ለመዋጋት ኃይላቸውን ለማሰባሰብ እንደሚያገደዱ አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን፣ አነስተኛና ቀላል የጦር መሳሪያ ዝውውርን እና የፈጠራ ፈንጂዎችን የመከላከልና የመዋጋት የፀና አቋም እንዳላትም መግለጫው አስምሮበታል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከወንድም የሶማሊያ ሕዝብ ጋር ከሰላም፣ ከመረጋጋት፣ ከምጣኔ ሀብታዊ እድገት እና ቀጣናዊ ትብብርን ከማስቀጠሉ ጎን እንደምትቆም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!