
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ እንደሚያካሂድ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አሳውቀዋል።
በጉባኤው የአስፈጻሚው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የዋና ኦዲተር እና የምክር ቤቱ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ክንውን ቀርበው ይገመገማሉ። የነዚሁ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት እቅዳቸውም ተገምግሞ ይጸድቃል፤ የተለያዩ አዋጆች እና ደንቦች ይጸድቃሉ፤ ልዩ ልዩ ሹመቶችም ይሰጣሉ ብለዋል።
አፈ ጉባኤ ፋንቱ በመግለጫቸው ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ተመራጮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን እና የመንግሥትን አቋም ማስረዳታቸውን ገልጸዋል። ለጉባኤ ሲመጡም የሰላምና የልማት እንቀስቃሴ መረጃ ይሰጣሉ፤ በክልላዊ ሁኔታዎችን ላይ ይወያያሉ፤ በቀጣይም የምክር ቤቱን ተግባሮች ወደ ሕዝብ ይወስዳሉ ነው ያሉት፡፡
የምክር ቤት አባላት ለሰላም በተደረጉ ኮንፈረንሶች የራሳቸውን ድርሻ እንደተወጡት ሁሉ በልማቱ ዘርፍም የተከናወኑ ሥራዎችን እንገመግማለን ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ። ተግባሮችን ከእቅድ ጀምረን እየተከታተልን እና ከሕዝብ ጋር እየተወያየን ለአስፈጻሚውም ግብረ መልስ እየሰጠን ነው ብለዋል። በቋሚ ኮሚቴዎች በተናጠልም በጋራም ክትትል በማድረግ እንዲሁም በ888 ነጻ የስልክ መስመር የሕዝብ አስተያየት በመቀበል ውክልናን ለመወጣት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልላችን የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሰላም አጀንዳን አስቀድመን በውይይት እና በድርድር ችግሮች እንዲፈቱ እንሠራለን ያሉት አፈጉባኤ ፋንቱ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል መንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ እያመቻቸ እና የተዋረድ ምክር ቤቶችም ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ አጀንዳ አድርገው እንዲወያዩበት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን በልማት ሥራ አተኩረን የ2016 በጀት ዓመት የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ ምክር ቤቶች ሕዝቡን ይዘው እንዲሠሩ እናደርጋለን ብለዋል። የ2017 እቅድም ሕዝብን አሳትፎ ውጤት በሚያመጣ መንገድ መታቀድ ስላለበት እና ባለፈው በጀት ዓመት የተንጠባጠቡ ሥራዎችን አሰባስቦ እንዲሠራ ምክር ቤቱ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
የምክር ቤት አባላትም ለመረጣቸው ሕዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ይጠበቃልም ብለዋል አፈ-ጉባኤዋ። የክልሉን ችግር ቀርፎ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እና ልማትን ማፋጠን የ2017 በጀት ዓመት ትኩረት ይኾናል። ኅብረተሰቡም በኀይል ብቻ የሚፈታ ችግር እንደሌለ በመረዳት ሁለቱም ኀይሎች ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ ጫና መፍጠር እንዳለበት አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡ ለሰላም ያሳየው ትብብር አበረታች ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የሕዝቡን ባሕል እና ታሪክ የሚያጎድፍ ሥራ መቃወም እና ማስቆም አለበት ብለዋል። የአማራን ሕዝብ መልካም እሴቶችን የሚሸረሽሩ ተግባሮችን ሁሉም ሊቃወም እና ሊያስቆም እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!