በግል ባለሃብቶች የሚለሙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች አሁን ላይ የት ናቸው?

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰፊ መሬት፣ በቂ የውኃ ሃብት ክምችት፣ አምራች የሰው ኃይል እና ለምርት ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት ኢትዮጵያ ግብርና የሕዝቦቿ የኑሮ መሠረት እና የጀርባ አጥንት እንደኾነ ይነገራል፡፡ “ግብርና ከማምረትም በላይ ነው” የሚለው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ቤተሰብ መሪ መልእክትም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሀገሬው ሕዝብ ቀዳሚ አጀንዳ ስለመኾኑ በቂ ምስክር ነው፡፡

በተለምዶ 85 በመቶ ሕዝቧ በግብርና ይተዳደራል የሚባልላት ኢትዮጵያ ግብርናዋ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ከበሬ እና ገበሬ፤ ከሞፈር እና ቀንበር ትከሻ ላይ ባይወርድም የግብርናው ዘርፍ አስፈላጊነት ግን ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከእነእጥረቱ እና ከነድክመቱም ቢኾን ግብርና አሁንም ድረስ የኢትዮጵያዊያን እስትንፋስ ነው፡፡

ወደ ኢንዱስትሪ መርነት መሸጋገርን መነሻው፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ደግሞ መዳረሻው ያደረገውን የግብርና ዘርፍ በግብዓት እና በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ወቅቱ የሚጠይቀው አርበኝነት እንደኾነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፉ የጀመረችውን አብዮት ዳር ለማድረስ ሁሉንም አቅሞቿን መጠቀም ግድ እንደሚላትም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለመኾኑ ከዓመታት በፊት በግል ባለሃብቶች የሚለሙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች አሁን ላይ የት ናቸው? በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ምርትና ምርታመነትን በማሳደግ በኩል የተሻለ ሚና አላቸው የሚባሉት አልሚዎች አሁን ላይ አበርክቷቸው ምን ይመስላል? በኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የግሉ ዘርፍ 12 ከመቶ ሰፋፊ እርሻ ያሥተዳድር እንደነበር ቢነገርም አሁን ግን ወደ 1 በመቶ ዝቅ ማለቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት እና በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት እና የሰላም እጦት ለዘርፉ መዳከም ከሚነሱት ቀዳሚ ችግሮች መካከል መኾናቸውም ይነገራል፡፡ አልሚዎችም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማበርከት የሚገባቸውን ማኅበራዊ ኀላፊነት አለመወጣት ሕዝቡ በባለቤትነት እንዳይመለከታቸው ማድረጉም ይነሳል፡፡

በአማራ ክልል ከጃዊ እስከ አየሁ፤ ከሕይዎት እስከ ብርሸለቆ፤ ከመተማ እስከ ከሚሴ በአልሚ ባለሃብቶች የተያዙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ያሉት ክልል ነው፡፡ ከሀገሪቷ ምርት 40 በመቶውን ገደማ ይሸፍናል የሚባልለት የአማራ ክልል በተለይም ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በማምረት በኩል ሰፊ አቅም አለው፡፡

ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን ይጠቀሳል፡፡ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ዞኑ በክልሉ ውስጥ በስፋት አልሚ ባለሃብቶች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው ይላሉ፡፡ አካባቢው በተለይም ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ አቅርቦት ተፈላጊ የኾኑ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና ሌሎችም የምርት ዓይነቶች የሚለሙበት አካባቢ እንደኾነ ይገልጻሉ፡፡

የሰሜኑ ኢትዮጵያ ግጭት እና እሱን ተከትሎ በተለይም በሱዳን አካባቢ የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ባለሃብቶች ያለስጋት እንዳያለሙ አድርጎ ነበር የሚሉት አቶ አንዳርጌ በመሠረታዊነት ለውጥ ባያመጣም እክል ፈጥሮ መቆየቱን ግን ነግረውናል፡፡ በአካባቢው ያለሙ ከነበሩ 900 አልሚ ባለሃብቶች መካከል በአሁኑ ጊዜ 500 ገደማ የሚኾኑት እያለሙ ይገኛሉም ብለውናል፡፡

በአካባቢው ከሚለማው 518 ሺህ 705 ሄክታር መሬት ውስጥም 121 ሺህ ሄክታር መሬት በአልሚ ባለሃብቶች ተይዞ እየለማ መኾኑን ነግረውናል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ እና የዞኑ ግብርና መምሪያም በግብዓት አቅርቦት፣ በገበያ ትስስር እና በሌሎችም መሠረታዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
አካባቢው ለሰፋፊ የእርሻ ልማት ምቹ አቅም ያለው ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ወደ አካባቢው ለሚመጡ አልሚዎች ተመራጭ እንደኾነም ነግረውናል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ሀገር በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ዘርፉ የሚጠበቅበትን እየሠራ አይደለም የሚሉት የኢትዮጵያ ሰብል አምራቾች እና ላኪዎች ባለ ብዙ ዘርፍ ማኅበር ፕሬዚዳንት መልካሙ አብርሃም ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ላይ በጸጥታ ችግር የተነሳ ጉዳት ደርሷልም ብለዋል፡፡

አቶ መልካሙ አሁንም ድረስ በጉዳት ምክንያት አገግመው ወደ ሥራ ያልተመለሱ የእርሻ ቦታዎች እንዳሉ ያነሳሉ፡፡ ከሰላም እጦቱ በተጨማሪም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ባለመጠቀም ምክንያት ምርት እና ምርታማነታቸው ዝቅተኛ መኾን፣ የባለሙያ እጥረት ማጋጠም፣ የብድር አገልግሎቱን በአግባቡ አለመጠቀም እና ሌሎችም ክፍተቶች ዘርፉን ወደ ኋላ ጎትቶታል ተብሏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፈረንሳይ የባቡር ትራንስፖርት ተቋረጠ።
Next article“በክልላችን የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሰላም አጀንዳን አስቀድመን በውይይት እና በድርድር ችግሮች እንዲፈቱ እንሠራለን” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ