
ወልድያ: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”በስፖርት እንቅስቃሴ በመተሳሰር ሰላም እና ወንድማማችነትን እንገባ” በሚል መሪ ሃሳብ ስፖርታዊ ውድድር በሀራ ከተማ ተካሂዷል። በሀራ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀው ውድድር በከተማዋ ወጣቶች እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ802ኛ ኮር ስፖርት ቡድን ጋር ነበር የተካሄደው።
የመክፈቻውን ጨዋታ ያደረጉት የሀራ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች ቡድን እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ802ኛ ኮር ቡድን ናቸው። ውድድሩ የተካሄደው ስፖርት ለጤና፣ ለሰላም፣ ለአንድነት ለፍቅር እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል እሳቤ ነው። በጨዋታው የኮሩ ከፍተኛ መሪዎች እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች ተሳትፈዋል። ውድድሩ 1 ለ 1 በኾነ ውጤት ተጠናቅቋል።
የሀራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሀመድ ሰዒድ ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በስፖርት ማዘውተሪያ እንዲያሳልፉ እንሠራለን ብለዋል። “ከምንወዳቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ይህንን ልዩ ጨዋታ በማድረጋችን ደስታ ተሰምቶኛል” ሲሉ ገልጸዋል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ802ኛ ኮር ዘመቻ ኀላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ ጥላሁን እንዳሉት ስፖርት ለወዳጅነት እና ለአንድነት ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ኮሎኔል ተስፋዬ ዛሬ ከሀራ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ጋር የተደረገው ጨዋታ አስደሳች እና ማራኪ እንደኾነም ነው ያብራሩት። በቀጣይ የመከላከያ ሠራዊቱ አባል በሌሎች መስኮች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ተሳትፎ ያደርጋል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!