“ስለሰላም መነጋገር ካልቻልን የአማራ ጥያቄዎችን እየፈታን ሳይኾን እያባባስን ነው የምንሄደው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

32

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የሴት ተመራጮች ፎረም ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሴት ተመራጮች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልእክት ያስተላለፉት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ውይይት የጋራ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። የሴት ተመራጮች ፎረም ሃሳብን የማስረጽ እና ተቀባይነት እንዲኖረው የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ገልፀዋል። የሚወጡ ሕጎችን አሳታፊነትን እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የሴቶች ፎረም የሴቶችን ውክልና ተሳታፊነት እንዲኖር ውይይት የሚደረግበት መኾኑን ገልፀዋል።

በተሠራው ሥራ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አለመምጣቱንም አንስተዋል። በቀጣይም መወያየት እና ግቦችን የሚያሳኩ መንገዶችን መተለም፣ መንገዶቹ ስኬታማ እንዲኾኑ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። በ2016 በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሴቶች ከማንም በላይ ተጎጂዎች እንዲኾኑ አድርጓል ብለዋል።

በሰላም እጦቱ ምክንያት ነጻ የሰዎች እና የሃብት ዝውውር የለም ያሉት አፈ ጉባኤዋ ነጻ ዝውውር ባለመኖሩ ግንባር ቀደም ተጎጂዎቹ ሴቶች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የሰላም እጦቱ በየቤታችን ከፍተኛ ችግር እያደረሰብን ነው ብለዋል። ሰላም እንዲመጣ ሴቶች የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።

እናቶች ልጆቻቸውን በመምከር፣ መልካሙን መንገድ በማመላከት፣ ለሕዝብ የሚጠቅመውን በማሳየት ትልቁን ድርሻ መውሰድ እንደሚገባቸውም አንስተዋል። ሴቶች ካላቸው ብልሃት እና ጥበብ እንጻር የችግሮች መፍቻ መፍትሔ መዘየድ እንደማይቸገሩም ገልጸዋል። ሰላም ባሕል ኾኖ እንዲቀጥል ለሰላም መዘመር እንደሚገባም አመላክተዋል።

ሰላምን ማጽናት ለመንግሥት ብቻ የሚሰጥ አለመኾኑንም ገልፀዋል። ሰላምን ለማስፈን ሁሉም በየተሰማራበት አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ነው ያሉት። ስለ ሰላም መነጋገር ካልቻልን የአማራ ጥያቄዎችን እየፈታን ሳይኾን እያባባስን ነው የምንሄደው ብለዋል። አሁን ያለው ግጭትም ችግሮችን ከመግታት ይልቅ እያባበሰ እና እያወሳሰበ እየሄደ መኾኑን ነው ያመላከቱት። በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አጋጥሞ የማያውቅ ችግር እያገጠመ፣ መልካም እሴቶች እየተሸረሸሩ መኾናቸውንም ገልፀዋል።

የማኅበረሰብ እሴት ፋይዳው ትልቅ መኾኑንም ተናግረዋል። በሰላም ዙሪያ በሰፊው መወያየት ይጠበቅብናልም ብለዋል። የክልሉን የሰላም ችግር ለመፍታት በክልሉ የሰላም ካውንስል መቋቋሙን የተናገሩት አፈ ጉባዔዋ የሰላም ካውንስሉ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ መንግሥት እና የታጠቁ ኃይሎች ወደ ንግግር እንዲመጡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መኾኑን ነው ያመላከቱት።

በየአካባቢያችን ጥያቄ አለኝ የሚልን አካል ወደ ውይይት እና ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ እንጂ ችግሩን መሸሽ መፍትሔ አያመጣም ነው ያሉት። ስለ ሰላም ለመነጋገር፣ ስለ ሰላም ድርድር እንዲደረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተቋቋመውን የሰላም ካውንስል መደገፍ ይገባል ብለዋል። የታጠቁ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የራስን ድርሻ መወጣት እንደሚገባም አመላክተዋል። ምክር ቤቱ ስለ ሰላም በስፋት እንደሚመክረም ገልጸዋል። ትልቁ አጀንዳችን ሰላም መኾን ይገባዋልም ብለዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ያነሱት አፈ ጉባዔዋ ልጆቻችንን ተወዳዳሪ ለማድረግ ስለ ሰላም በትኩረት መሥራት አለብን ነው ያሉት። የልጆቻችን አለመማር ካልቆጨን የሚቆጨን ነገር የለም ብለዋል። ትምህርት ላይ የሚገጥመው ስብራት ነገ እና ከነገ ወዲያ ለሚደረገው ውድድር አሉታዊ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ነው ያመላከቱት።

የአማራን ጥያቄ መሠረት ያደረገ ትግል እየተደረገ ነው፤ በክልሉ መፈታት የሚችሉ በክልሉ ይፈታሉ፤ የሌሎች አካላትን እገዛ የሚፈልጉትም በሚፈቱበት መንገድ ይሠራል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በቅርብ ዓመታት ባልታየ መልኩ የወባ ሕሙማን ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ፡፡
Next article“ለምግብ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የሀገራችንን እድገት ማረጋገጥ ይገባናል” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)