
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ እንደተያዙ በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የወባ ፕሮግራም አሥተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንከር ገልጸዋል፡፡
አቶ ዳምጤ እንዳሉት የወባ ሥርጭቱ በምዕራቡ የክልሉ ክፍል በሚገኙ ዞን እና ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል፡፡ እነዚህ ዞኖች 90 በመቶ የክልሉ የወባ ሥርጭት የታየባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
በተለይ ባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ደንቢያ፣ ጎንደር ዙሪያ እና ሌሎችም ወረዳዎች 71 በመቶ የሚኾነውን የወባ ሥርጭት እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳምጤ የወባ ሥርጭቱ በቅርብ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያልታየ ነው ይላሉ። በሳምንት 43 ሺህ ሕሙማን ሪፖርት ይደረጋል፤ ይህ በክረምት ወቅት ከ10 ዓመት በፊት ተከስቶ የነበረ ነው ብለዋል፡፡ ወደፊት በዚህ ከቀጠለ መስከረም እና ጥቅምት ላይ 90 እና መቶ ሺህ ሕሙማን ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ ማኀበረሰቡ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ማጠናከር፣ የታቆሩ የውኃ ቦታዎችን ማፋሰስ እንዲሁም ማዳፈን ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ዳምጤ አያይዘውም በተለይ ለግንባታ ተብለው የሚሠሩ የኮንክሪት የውኃ ማጠራቀሚያዎች ከፍተኛ የኾነ የትንኝ መራቢያ በመኾናቸው ግንባታው ከቆመ በኋላ ባዶ እንዲኾኑ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የአጎበር አጠቃቀም ባሕላችንን ማሳደግ፣ የሕመም ስሜት ሲሰማ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እና የታዘዘውን መድኃኒት ሳያቆራርጡ መውሰድ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የወባ ፕሮግራም አሥተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንከር ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት እና የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ በተቀናጀ መልኩ የወባ ሥርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ እንደኾነም አስረድተዋል።
በተለይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት፣ ግብዓት በማሟላት፣ የርጭት ሥራ እንዲከወን በማድረግ፣ ኅብረተሰቡ የአጎበር ተጠቃሚ እንዲኾን በማገዝ እና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲጠናከር የማድረግ ተግባር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!