“የሀገሪቱ የጋራ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለማበጀት የአካል ጉዳተኞችም መምከር አለብን” ዋና ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ

30

አዲስ አበባ: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እና ሚና ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሂደቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመኾን ለምክክሩ ዋነኛ አጀንዳዎች ባለቤት እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ተብሏል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን ጨምሮ ሌሎች የኮሚሽኑ የሥራ ኀላፊዎች እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ ተገኝተዋል።

ሀገሪቱ ውስጥ በሚስተዋሉ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ሁሉም ማኅበረሰብ ተጎጅ ቢኾንም በአካል ጉዳተኞች ደግሞ የከፋ ውጤት ይኖረዋል ያሉት የኢትዮጵያ አካልጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ ናቸው። “የሀገሪቱ የጋራ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለማበጀት የአካል ጉዳተኞችም መምከር አለብን” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት እና የዜግነት መብታቸውን ለመጠቀም በምክክር ሂደቱ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞች በምክክሩ መሳተፋቸው የሂደቱን አካታችነት የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ናቸው። በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች አብዛኛው መነሻቸው ባለፈ ትርክት ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ይህን የዘመናት ችግር ማከም የሚቻለው በምክክር ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በሚያጋጥሟት ተደጋጋሚ ግጭቶች እና ጦርነቶች የአካል ጉዳተኞች የበለጠ ተጎጅ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ በየጊዜው ተጨማሪ አካል ጉዳተኞች እንዲፈጠሩም ምክንያት ሲኾኑ ተመልክተናል ነው ያሉት። የአካል ጉዳተኞች ችግር ለማቃለል እና በግጭት ምክንያት ሌሎች አካል ጉዳተኞች እንዳይፈጠሩ መመካከር እና የሰላም መፍትሄ ማምጣት ብቸኛው አማራጭ ነው ብለዋል።

በመኾኑም የምክክር ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ እና የአካል ጉዳተኞችን ሃሳብ ለማካተት የምክክር ሂደቱ አካል መኾን እንዳለባቸው ነው ዋና ኮሚሽነሩ የተናገሩት። የአካል ጉዳተኞችም ያሏቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች በማሰባሰብ እና ወደ ምክክሩ በማምጣት ሀገራዊ ተሳትፎ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አደራው ምንውዬለት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ መርሐ-ግብር እያካሄደ ነው፡፡
Next article“ኢትዮጵያ የወንዞች ሀገር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ