
በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የተመራ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቡድን የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን የግንባታ ሂደት ትናንት ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ የተገኙ የቋሚ ኪሚቴ ሰብሳቢዎች እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት ስታዲየሙ ከስፖርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል። ስታዲየሙ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ነው የምክር ቤት አባላቱ የገለጹት። በምክር ቤቱ የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ደምስ እንድሪስ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የስፖርት ቱሪዝም ዘርፉ እንዲያድግ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
በአማራ ክልል እንዲያድግ ከሚፈለገው ጉዳይ አንደኛው ቱሪዝም መኾኑንም አንስተዋል። ስፖርት ቱሪዝምን ከማሳደግ አኳያ የስታዲየሙ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አመላክተዋል። የባሕር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ኾኖ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ እና ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል ነው ያሉት።
የስፖርት ቱሪዝም እንዲስፋፋ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ስፖርት የክልሉን የቱሪዝም ሃብት በማሳደግ በኩል ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት። ክልሉን በማስተዋወቅ፣ የክልሉን ገጽታ የበለጠ በመገንባት እና ወጣቶችን ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመሳብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት። ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያለው ስታዲየም በፍጥነት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾን እንፈልጋለንም ብለዋል። ስታዲየሙ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት እና ባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባል አሊ ይማም ስታዲየሙ ለመዝናኛ የሚኾኑ ሥራዎችን በውስጡ በመያዙ ጎብኚዎችን ይስባል ነው ያሉት። ስታዲየሙ የከተማዋን የእድገት ደረጃ ማሳያ መኾኑንም ገልጸዋል። ስታዲየሙ ለወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል። የሰው ሃብት እና የቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ ስታዲየሙ ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ታላቅ የገበያ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ ኾኖ እንደሚያገለግልም ገልጸዋል።
የግንባታ ሂደቱ በቶሎ ተጠናቅቆ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ሲጀምር ለክልሉ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝም አንስተዋል። ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል። የሕግ ፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ስታዲየሙ ከስፖርት ባሻገር ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። አሕጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሚያስተናግድበት ጊዜ የሚቀበላቸው እንግዶች የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ እንደሚያደርጉ ነው ያመላከቱት።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች፣ ስፖርተኞች እና ደጋፊዎች እንዲመጡ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በውስጡ በያዛቸው ሃብቶች ከእግር ኳስ ባለፈ የሕዝብ መዝናኛ ማዕከል ኾኖ እንደሚያገለግልም ተናግረዋል። የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እመቤት ከበደ ስታዲየሙ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በምጣኔ ሃብት በኩል ለአማራ ሕዝብ ያስፈልገዋል ነው ያሉት። ከስፖርት ያለፈ ብዙ አንድምታ ያለው ፕሮጀክት መኾኑንም ገልጸዋል።
የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ መጠናቀቅ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ፕሮጀክቶች በተጓተቱ ቁጥር በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሙም አንስተዋል። በክልሉ ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እና የስብዕና መገንቢያ ቦታዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!