
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የግብርና ዘርፍ ክላስተር በ2016 የበጀት ዓመት የተሠሩ ሥራዎችን እየገመገመ ነው።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በዓመቱ በክልሉ የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ቢከሰቱም በክላስተሩ ሥር የተደራጁ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
የጸጥታውን ችግር በመቋቋም ታች ድረስ ወርደው ከኅብረተሰቡ ጋር በመገናኘት የልማት ፍላጎቶችን በመለየት፣ ጉድለቶችን በመሙላት እና አንገብጋቢ ችግሮችን በመፍታት በኩልም ሰፊ ትምህርት የተገኘበት ዓመት ነበር ብለዋል።
በመኾኑም ”በጸጥታ ችግርም ውስጥ ኾነን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሠርተናል” ብለዋል።
በ9 ዞኖች፣ 43 ወረዳዎች እና በ429 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ የሰው ሕይዎት እንዳይጠፋ መንገድ በሌለባቸው አካባቢዎች 270 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በመሥራት፣ የመጠጥ ውኃ ተቋማት በወደሙባቸውም አካባቢዎች ጥገና በማድረግ፣ ለመስኖ ዘር እና ማዳበሪያ በማቅረብ የክላስተሩ ተቋማት በቅንጅት መረባረባቸውን ገልጸዋል።
በማዕድን ዘርፍ የተደረገው ድጋፍ ሰፊ እመርታ የታየበት ነው ብለዋል። በእንስሳት ዘርፍ በሌማት ቱሩፋት ተግባራትም የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ገበያ የሚያረጋጋ ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በችግር ውስጥ ኾኖ የሕዝብን ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉ ጥንካሬ እንደኾነ ያነሱት ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የገጠመንን የሰላም ችግር በፍጥነት መቀልበስ አለመቻላችን እንደ ድክመት ይወሰዳል ብለዋል።
የግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አጀበ ስንሻው ባለፈው በጀት ዓመት በግብርና ልማቱ የአረንጓዴ አሻራ፣ የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት፣ የመካናይዜሽን እና የሰብል ልማት ሥራዎች ጎልተው የወጡ ተግባራት መኾናቸዎን ገልጸዋል።
በሰብል ልማት 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኅላፊው እስካሁን 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
አርሶ አደሩ ማግኘት የሚገባውን ማዳበሪያ በመጠንም በጊዜም ማግኘቱን የገለጹት አቶ አጀበ 8 ሚሊዮን 58 ሺህ ኩንታል የሚኾን ማዳበሪያ ተገዝቶ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወደብ ላይ መድረሱን፣ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዩኒየኖች ላይ መግባቱን እንዲሁም 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚኾነው መሠራጨቱን አብራርተዋል።
”ባለፈው ዓመት ከተሠራጨው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጋር ሲነጻጸር ታላቅ ብልጫ ያለው እና ምርት የሚጨምር ነው” ብለዋል። ከታቀደው 188 ሺህ ኩንታል የምርጥ ዘር ሥርጭት ውስጥ 142 ሺህ ኩንታሉን ማሠራጨት መቻሉንም እንደ ስኬት አንስተዋል።
በመስኖ በኩል 233 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ 90 በመቶው መሳካቱን ተናግረዋል። በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በኩል ደግሞ ከታቀደው 56 በመቶው መከናወኑን ገልጸዋል። ጎን ለጎንም የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማከናወን 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 1 ነጥብ 44 ቢሊየን ችግኝ መትከል መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!