“ዞኑ ከ80 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የጉልበት ሠራተኛ ለወቅታዊ የግብርና ሥራ ይፈልጋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን

19

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን ለምግብ፣ ለኢንዱስትሪ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ሰብሎች በስፋት እየለሙ ይገኛሉ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድልቃድር በዘንድሮው የሰብል ልማት 561 ሺህ 856 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑ ገልጸዋል፡፡

ቡድን መሪው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 533 ሺህ 763 ሄክታር መሬት በሰብል እንደተሸፈነ ነው ያብራሩት፡፡

ወቅቱ አረም በስፋት የሚታረምበት ወቅት መኾኑን የገለጹት አቶ ኑርሁሴን ለዚህም ከ80 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ባለሃብቶች በትንሽ የሰው ኀይል ሰብላቸውን እያሳረሙ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት፡፡ የለማው ሰብል ውጤታማ እንዲኾን በርካታ የጉልበት ሠራተኞች የሚያስፈልጉ በመኾኑ ሠራተኞች ወደ አካባቢው በመምጣት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመንም ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ በዕቅድ መያዙን ነው ያስረዱት።

በአካባቢው ያሉ ባለሃብቶች ለጉልበት ሠራተኛው የሚኾን የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የወባ መከላከያ አጎበር፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ መድኃኒት እና ሌሎች አሰፈላጊ ግብዓቶችን ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው ሠራተኛ በቂ እንዳልኾነ በአካባቢው በልማት ላይ የተሰማሩት አልሚ ባለሃብት አቶ ካሳሁን ተድላ አስረድተዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የጉልበት ሠራተኛ እጥረት ሰብላቸውን በጊዜው መንከባከብ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ነው ያብራሩት፡፡ አቶ ካሳሁን ከ80 ሄክታር መሬት በላይ በሰሊጥ ሰብል መሸፈናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሰብል ሲያርሙ ያገኘናቸው የጉልበት ሠራተኛ ወጣቶች በቀን እስከ 600 ብር ድረስ እየተከፈላቸው እየሠሩ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት፡፡ የምግብ እና የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትም በጥሩ ሁኔታ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ዞኑ ሰላም በመኾኑ ሠራተኞች ወደ አካባቢው በመምጣት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ መቅረቡን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶአደሮች ማሳ ደርሷል” ግብርና ቢሮ
Next article”በጸጥታ ችግርም ውስጥ ኾነን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሠርተናል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)