“ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶአደሮች ማሳ ደርሷል” ግብርና ቢሮ

18

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016/2017 የመኽር ምርት ዘመን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል።

በምርት ዘመኑ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው አብራርተዋል፡፡ ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 3 ሚሊዮን 117 ሺህ 20 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ቀሪውን መሬትም በዘር ለመሸፈን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡

አቶ አምሳሉ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያን ከመጠቀም ባለፈ በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ በሰፊው እየተሠራ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት። 6 ሚሊዮን 286 ሺህ 268 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖች ስለመግባቱ ገልጸዋል፡፡ ከ6 ሚሊዮን 127 ሺህ 497 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አረሶ አደሮች ማሳ መድረሱንም አቶ አምሳሉ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከመጠቀም ባለፈ አርሶ አደሮች መደበኛ ኮምፖስት በመጠቀም እንዲያመርቱ 102 ሚሊዮን 31 ሺህ 197 ሜትር ኩብ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በዕቅድ ተይዞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 59 ሚሊዮን 503 ሺህ 665 ሜትር ኩብ ኮምፖስት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ የተዘጋጀው ኮምፖስት 1 ሚሊዮን 630 ሺህ 313 ሄክታር መሬት ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

አቶ አምሳሉ ቢሮው ለ2016/2017 የምርት ዘመን 509 ሺህ 612 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማምረት ከአርሶ አደሩ እና ከባለሃብቱ ጋር በመቀናጀት ለመሥራት ዕቅድ እንደተያዘ ነው የገለጹት፡፡ ክልሉ ካለበት አሁናዊ የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተዘዋውሮ እገዛ ለማድረግ ተግዳሮት ቢኖርም በስልክ፣ በሬዲዮ እና በተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ምክረ ሃሳብ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት

አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጠው ምክረ ሃሳብ መሠረት የዘር ሥራውን ከማከናወን ባለፈ በቀጣይ የአረም እና የተባይ ክትትል ሥራ በማከናወን ዕቅዱ እንዲሳካ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የባሕር ዳር ስታዲየምን እየጎበኙ ነው።
Next article“ዞኑ ከ80 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የጉልበት ሠራተኛ ለወቅታዊ የግብርና ሥራ ይፈልጋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን