
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አማካኝነት በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ መሳቢያ ሞተር ለመስኖ አልሚ አርሶ አደሮች በረጅም ጊዜ ብድር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሠራው የውኃ መሳቢያ ሞተር የክልሉ ግብርና ቢሮ ሽድፒ ከሚባል አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር በረዥም ጊዜ የብድር ሥርዓት የቀረበ መኾኑ ተገልጿል። የዞኑ የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ አዲስዓለም ቢተው እንዳሉት የመስኖ አልሚ አርሶ አደሮቻችን ጥያቄ ለነበረው ችግራቸው ምላሽ የሰጠ ብለዋል። ለክልሉ ግብርና ቢሮ እና አጋር ድርጅቶች ምሥጋና እናቀርባለን ነው ያሉት።
ለልማቱ ማነቆ ኾኖ የቆየው የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና በፈለጉት ጊዜ አለመገኘት በከፍተኛ ሁኔታ ፈታኝ መኾኑንም ቡድን መሪው አንስተዋል። በሁለት ወረዳዎች እና በአንድ ከተማ አሥተዳደር በመጀመሪያ ዙር የመጡ ሞተሮችን አሰራጭተናል፤ የተከላ እና የመገጣጠም ሥራዎችንም አብረን እያስተባበርን እንገኛለንም ብለዋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን በረጅም ጊዜ ብድር ተጠቃሚ የኾኑት የገንደ ውኃ ከተማ የመስኖ አልሚ አርሶ አደር አሊ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመኾናቸው መደሰታቸውን የዞኑ ኮሙኑኬሽን መረጃ ያሳያል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!