“በሀገረ-መንግሥት ግንባታም ኾነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንሠራለን” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሲሠራበት የቆየውና ዜጎችም ሲጠየቁ የኖሩት በሀገራዊ ምክክር አማካኝነት መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሳቤ አሁን ላይ ወሳኝ ሊባል በሚችል ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገረ-መንግሥት ግንባታም ኾነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ መድረኮችን ሲያመቻችና የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

እንደሀገር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች መኾናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፆ ስለሚያበረክት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ካለፈው መጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት በስምንት ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን በመጠቆም ለዚህም ምሥጋና አቅርበዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ “አሸናፊ ኾነን እንውጣ ከተባለ መመካከር አለብን በምክክሩም ሴቶችን ይዘን መውጣት አለብን። የሴቶች አጀንዳ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነው” ብለዋል።

የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ፕሬዝዳንት ሳባ ገብረ መድህን በሀገራዊ የምክክር መድረክ በሴቶች ተገቢውን ውክልና አግኝተው የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱና በሀገሪቱ የወደፊት እድል ላይ እንዲወስኑ ማድረግ መኾኑን ስለመጥቀሳቸው ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማኅበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ249 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleበፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ መሳቢያ ሞተር ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ተደረገ።