
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዘውላ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር አደራው ሉሌ ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ እጥረት እና ሕገ ወጥ ግብይት ስለነበር በሚፈልጉት ልክ የማዳበሪያ ግብዓት መጠቀም አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ምርታቸው አንደቀነሰ እና ሕገ ወጥ ግብይቱም ላልተፈለገ ወጭ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ አደራው በዚህ ዓመት በቂ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ወቅቱን ጠብቆ በማኅበራት በኩል ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሃሳብ በመቀበል 12 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ120 እስከ 140 ኩንታል ምርት ለማምረት በማቀድ እየሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው በ2016/2017 የመኸር ምርት ዘመን ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቀዶ 249 ሺህ 850 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቋል፡፡ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በምርት ዘመኑ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተር እና የሩዝ ዘርን ለመዝራት አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ዕቅዱን ለማሳካትም ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እና 536 ሺህ 899 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማሰራጨት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲኾን መደረጉን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡
በዚህም 203 ሺህ 824 አርሶ አደሮችን ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ምርት ለማምረት ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በመኸር ወቅት 164 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በመስኖ የተዘራ ሲኾን በመስመር፣ በኩታ ገጠም መዝራት እና የተሻሻሉ አሠራሮችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
በ2016/2017 የምርት ዘመኑ 14 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የተሻለ ምርት ለማግኘትም አርሶ አደሮች ወቅቱን ጠብቀው ደጋግመው እንዲያርሱ ምክረ ሃሳብ በመስጠት፣ የምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያን በማሰራጨት የግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እንዲሁም ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!