
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ልማት ማኀበር (አልማ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት 74 የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሠራ መኾኑን አስታወቋል።
ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ8 መቶ 80 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት መሰብሰቡንም አስታውቋል። በዚህም ከ318 በላይ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለማኀበረሰቡ ማስረከቡን በአማራ ልማት ማኀበር የምሥራቅ ጎጃም ዞን አልማ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ዘላለም አንዳርጌ ተናግረዋል።
ከተመሠረተ 32 ዓመታት ያስቆጠረው የአማራ ልማት ማኀበር (አልማ) በክልሉ በተለይም በማኀበራዊ ልማት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ልማት ማኀበሩ ውጤማ እንዲኾን የዞኑ ማኀበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የጉልበት፣ የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ዘላለም አሁንም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ጫና ቢያሳድርም ችግሩን ተቋቁመው ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውንም ኅላፊው ተናግረዋል።
የአማራ ልማት ማኀበር (አልማ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ655 ሺህ በላይ አባላት እና ከ16 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በመያዝ የዞኑንን ማኀበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ከዞኑ አልማ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!