“ከዳግም ምርጫ እራሴን ያገለልኩት ለፓርቲው እና ለሀገሬ አንድነት በማሰብ ነው” ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከ2024 ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ለአሜሪካ ሕዝብ የመጀመሪያውን ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም በዴሞክራት እጩነታቸው ለምን መቀጠል እንዳልፈለጉ እና ምክትል ፕሬዚዳንት የኾኑትን ካሜላ ሀሪስን እንዴት እንደተኳቸው ሰፊ ንግግር አድረገዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “ከዳግም ምርጫ እራሴን ያገለልኩት ለፓርቲው እና ለሀገሬ አንድነት በማሰብ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም ለአዲስ ድምጽ እና ለወጣት ጉልበት ጊዜ እና ቦታ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ፕሬዚዳንቱ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶናልድ ትራምፕ ባይደን በምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኃላ የመጀመሪያ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ዛሬ አድርገዋል። በቅስቀሳቸውም “ባይደን ከምርጫ የወጣው እየተሸነፈ ስለነበር ነው” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሕዳር 2024 የሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአጓጊነቱ እንደቀጠለ ነው። አሜሪካ በዓለም ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት ደግሞ የምርጫው ውጤት ከአሜሪካ አልፎ በዓለምም እንዲጠበቅ ያደርገዋል። በተለይ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ በጋዛ ጦርነት፣ በቻይና የንግድ እንቅስቃሴ፣ በስደተኞች እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚይዘው አቋም ምርጫው በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲጠበቅ አድርጎታል ይላል ቢቢሲ።

ዶናልድ ትራምፕ የመራጮችን ድምጽ ለማግኘት ከሚታገሉበት አጀንዳ መካከል አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነው። እንደ ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ወል ስትሬት ጆርናል ዘገባ የስደተኝነት ጉዳይ የመራጮችን ድምጽ የሚወስን ትልቅ ነጥብ ነው። “አሜሪካውያን ከሥራ ውጭ የኾናችሁት በመጤዎች ነው” በማለት የሚሰብኩት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን በተመለከተ የጥላቻ ንግግራቸውንም ቀጥለውበታል። ይህ ንግግራቸው በመራጮች ዘንድ ተቀባይነታቸውን ከፍ እንዳደረገው ጥናቶች አመላክተዋል።

በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከዴሞክራቷ ጥቁር ተቀናቃኛቸው ካሜላ ሀሪስ ጋር ሰፊ የሃሳብ ልዩነት እንደሚያንጸባርቁ ይጠበቃል። ወትሮውንም ቢኾን ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ የሌላቸው ስደተኞች ድምጻቸውን ለዲሞክራቷ ካሜላ ሀሪስ እንደሚሰጡ የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ ይጠቁማል። የጃማይካ እና ሕንድ ዝርያ ያላቸው ካሜላ ሀሪስ በተለይ በእስያውያን እና ጥቁር መራጮች ዘንድ ሰፊ ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡
Next articleየአማራ ልማት ማኀበር (አልማ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን 74 የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ፡፡