
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣንን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ ባቀረቡት ሪፖርት በቁልፍ ተግባርነት የተከናወኑ እና ለዐበይት ተግባራት መፈጸም እና ስኬት የሚያገለግሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ዘርዝረዋል፡፡
ከእነዚህ ውስም በጸረ ሌብነት ትግል ከተሸከርካሪ እና ትራንስፖርት ጋር የተገኙ ሀሰተኛ መረጃዎችን መቆጣጠር፣ የማሠልጠኛ ተቋማትን ደረጃ ማብቃት እና መቆጣጠር፣ የመነኻሪያ አገልግሎትን የማሻሻል ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት፣ የሥራ ቦታን ማመቻቸት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የማሠልጠን፣ ለዞኖች የበጀት ድጋፍ የማድረግ፣ መመሪያዎችን የማውጣት፣ መልካም አሥተዳደርን የማስፈን እና የተገልጋይን እንግልት እና ብዝበዛ የመቀነስ ሥራ መሠራቱ ተመላክቷል፡፡
የበጀት ዓመቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 72 በመቶ መኾኑንም ኀላፊው ጠቅሰዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ፣ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ መረጃን በመያዝ፣ የደሴ መነኻሪያን እድሳት ጨምሮ የሕዝብ ትራንስፖርት መነኻሪያዎችን ወደ 264 በማሳደግ እንዲሁም የትራፊክ ኮምፕሌክሶችን የመገንባት ሥራ መሠራቱን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
የትራንስፖርት ማኅበርን በማጠናከር፣ የብቃት ማረጋገጫ እንዲታደስ በማድረግ፣ 36 አዲስ የትራንስፖርት መስመሮችን በመክፈት፣ ተሽከርካሪዎችን በተደጋጋሚ ሥምሪት በመስጠት ሕዝብን የማጓጓዝ ሥራ መሠራቱም ተገልጿል፡፡ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አኳያም አሽከርካሪዎች የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ዕውቀት ኖሯቸው መንጃ ፈቃድ እንዲያገኙ ለማድረግ የአሠራር እና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አብራርተዋል፡፡ የተሸከርካሪ ደኅንነት ምርመራ (ቦሎ) 72 በመቶ መከናወኑም ተጠቅሷል፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመከላከልም የማሠልጠን፣ የራዳር እና የመደበኛ ቁጥጥር መደረጉ ተገልጿል፡፡ በሰው አካል እና ሕይዎት እንዲሁም በንብረት ላይ ይደርስ የነበረ አደጋ በ2015 በጀት ዓመት 1 ሺህ 915 የነበረውን አጠቃላይ አደጋ በ2016 በጀት ዓመት ወደ 980 መቀነስ መቻሉ ተመላክቷል፡፡በተሽከርካሪ ድንገተኛ ምርመራ፣ የመናኻሪያ፣ የማሠልጠኛ ተቋማትን፣ የኦፕሬተር ፈቃድን በመመርመር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ጉድለት የተገኘባቸው መቀነሱ ተመላክቷል፡፡
በክልሉ የሎጀስቲክስ አገልግሎት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገባ ክትትል መደረጉ፣ ለጭነት ተሸከርካሪ 15 ተርሚናሎች ተለይተው መሬት እየተዘጋጀ መኾኑንም አቶ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የኅብረተሰብ ተሳትፎ፣ የነዳጅ ድጎማ ሥራ፣ የባለ ብዙ ዘርፍ ጉዳዮችም በትኩረት መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት ተንቀሳቅሶ ሕግ ለማስከበር አለመቻሉ እና የሹፌሮች እገታ፣ በብልሹ አሠራር ውስጥ ያሉ አካላት የኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት እንዳይጀመር እንቅፋት መኾናቸው ጉልህ እንቅፋቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ ተወያዮች በሰጡት አስተያየት በቴክኖሎጂ የአገልግሎት ማሳለጥ ሥራን አበረታትተዋል፡፡ የመናኻሪያ አገልግሎት አሰጣጥ ሕዝብ የሚንገላታበት ስለኾነ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በጽሑፍ በሰጠው ግብረ መልስም
👉 የተሽከርካሪ ቁጥጥር በማድረግ ሕግ ለማስከበር የተጀመረው ሥራ
👉 የተዋረድ ተቋማትን ለማጠናከር የተሠራው ሥራ
👉 የመነኻሪያዎችን ደረጃ ለማሳደግ እና ምቹ ለማድረግ እንዲሁም አደጋን ለመቀነስ የተሠራው ሥራ በጥንካሬ የተነሱ ናቸው።
በእጥረት ከተነሱት ውስጥ፦
👉 የሚወጡ ሕጎችን በሁሉም አካባቢዎች በወጥነት አለመተግበር
👉 ብልሹ አሠራር በፈጸሙ ባለሙያዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በሁሉም ዞኖች ተግባራዊ አለመኾን
👉 ኢ-ቲኬቲንግ ወደ ሥራ ለማስገባት መዘግየት
👉 የራዳር መቆጣጠሪያ በሁሉም አካባቢ አለማዳረስ እና የሽፋኑ አነስተኛነት
👉 በባሕር ዳር እና መሰል ከተሞች የታክሲ አገልግሎት ታሪፍን መቆጣጠር ላይ ውስንነት መኖር የሚሉት ይገኙበታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!