የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ።

35

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የቢሮውን የሥራ አፈጻጸም የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሀመድ (ዶ. ር) አቅርበዋል። ባቀረቡት ሪፖርትም እንዳሉት፡-

👉 የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ
👉 የንግድ ሥርዓቱን ሕጋዊ ማድረግ እና ማስፋት
👉 የግብይት ተዋናዮችን አቅም በሁሉም ረገድ በማሳደግ ኑሮ ውድነትን ማረጋጋት
👉 አምራች እና ሸማችን የሚያገናኙ የግብይት ማዕከላትን መገንባት
👉 አስገዳጅ ምርቶች ግብይትን ከ4 ነጥብ 5 ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራቱን አንስተዋል፡፡

329 ሺህ የኦንላይን አገልግሎት መሰጠቱን፣ በበር ለበር የንግድ ድርጅቶች ቁጥጥር መደረጉን፣ ሕጋዊነትን ለማስፈን መሠራቱን፣ ሕጋዊ የንግድ ሽፋንን ወደ 54 በመቶ ማሳደግ መቻሉን፣ የውል እርሻ ግብይት በማድረግ እና በማስመረት 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት (ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና ቦለቄ) ወደ ዉጪ መላኩን አስረድተዋል፡፡

አምራች እና ሸማች በቀጥታ የሚገናኙበት 11 የምግብ ፍጆታ ገበያዎች እና 113 ልዩ ገበያዎች መቋቋማቸው እንዲሁም 60 አዲስ ገበያዎችን በማቋቋም እና 938 ነባር ገበያዎችን የማጠናከር ሥራ መሠራቱን፣ ዋና ዋና የገበያ ተዋናዮችን በማስተሳሰር 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መሠራቱን አብራርተዋል። በተመቻቸው ብድር 713 ሺህ ኩንታል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ማቅረብ መቻሉም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ በተሠራው ሥራም በሰብል፣ በአትክልት እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ መረጋጋት መፈጠሩ እና በታኅሣሥ 2016 ዓ.ም ከነበረው ዋጋ ሲነጻጸር ከ5 እስከ 31 በመቶ የዋጋ ቅናሽ መኖሩን ዶክተር ኢብራሂም አመላክተዋል። የኑሮ ውድነቱን ግምት ውስጥ ያስገባ ሕጻናት እና ችግረኞችን የመርዳት፣ ለሠራተኞች ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ካፌ መክፈት፣ የሕጻናት ማቆያ ማዘጋጀት፣ የሸማቾች ማኅበር የማቋቋም ሥራም መሠራቱን ኀላፊው ጠቁመዋል።

በኋላ ቀር አስተሳሰቦች መታጠር፣ ቅንጅታዊ አሠራር በቂ አለመኾን፣ የምርት ማስተሳሰር በበቂ መጠን አለመፈጸም፣ ሕገ ወጥ ንግድን በበቂ አለመታገል ውስንነቶች እንደነበሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል። በውይይቱ ቢሮው የነዳጅ አቅርቦት እንዳይቆም ጥረት ማድረጉ እና የፍጆታ ሸቀጦችን ለማቅረብ የጀመረው ሥራ ጥሩ መኾኑ ተገልጿል። በአንጻሩ ደግሞ ሕገ ወጥ ንግድን ያለ ድርድር አጥብቆ እንዲታገል፣ ደረሰኝ አለመስጠትን እና ጊዜው ያለፈበት ምርትንም እንዲቆጣጠር አስተያየት ተሰጥቷል።

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ክትትል መሠረትም በጥንካሬ ያያቸው ሥራዎች ላይ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡-

👉 የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ማኅበራትን በማጠናከር ብድር ማቅረቡ
👉 ሕገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር መጀመሩ
👉 የንግድ ቅሬታዎችን ለመፍታት አሠራር መዘርጋቱ
👉 ሰሊጥ እና ሌሎች ጥራጥሬዎችን ወደ ውጪ መላክ መቻሉ
👉 በጸጥታ ችግር ወደ አዲስ አበባ መላክ ያልተቻለውን የወተት ትስስር በመፍጠር ለከተሜው እንዲቀርብ መደረጉ
👉 ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ችግረኞችን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራ መሠራቱ በጥንካሬ የተጠቀሱ ናቸው።
በቀጣይ በትኩረት እንዲሠሩ አስተያየት ከተሰጠባቸው መካከል ደግሞ፡-
👉 ኾን ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውልን የማጭበርበሪያ የመለኪያ መሣሪያን ለመከላከል የጥቆማ ሥርዓት አለመኖሩ
👉 ሕጋዊ ደረሰኝ በማይሰጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተደረገው ጥረት አነስተኛነት
👉 የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ለመከላከል የተሠራው ሥራ አነስተኛነት
👉 የመሠረታዊ ሸቀጥ (ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ቤንዚን) አቅርቦት አነስተኛ መኾን
👉 የንግድ ቁጥጥሩ ተከታታይ እና ወጥ አለመኾን
👉 የሸማች ማኅበራትን የብድር እና የመሸጫ ቦታ ችግር በዘላቂው አለመፍታት ሊታዩ የሚገባቸው ናቸው ብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎርፍ አደጋ ስጋት እንዳለባቸው የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
Next article“ያለፈው በጀት ዓመት ጥንካሬ እንደ መስፈንጠሪያ ድክመቶችን ደግሞ ለማረም ያስችላል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)